በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሀገሪቱን ህግና ሉዓላዊነት የማክበር ግዴታ አለባቸው

121

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሀገሪቱን ህግና ሉዓላዊነት የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከተደረገ በኋላ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማስፈፀም የሚችሉበት ሰፊ ምህዳር ተፈጥሯል፡፡

በተለይ የሲቪል ማህበራትና ድርጅቶችን በሚመለከት የተደረገው የአዋጅ ማሻሻያ በዘርፉ የተሻለ የአሰራር እንዲኖር ማስቻሉንም ነው ያነሱት፡፡

በመሆኑም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ደግሞ በአስረጂነት ጠቅሰዋል፡፡ 

መንግስት እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች የፈጠረ ቢሆንም አንዳንድ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህግን ያለማክበርና ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ እንደሚታዩ ተናግረዋል። 

በተለይ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያይዞ አንዳንድ የውጭ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በርካታ የህግ ጥሰቶችን እንደሚፈጽሙ ነው ያነሱት።

"ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ነች፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሀገሪቱን ህግና ሉዓላዊነት አክብረው የመንቀሳቀስ ግዴታ እንዳለባቸው" ብለዋል

ባለስልጣኑ ከአሁን በፊት ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ባገኛቸው ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱንም  ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም መሰል የህግ ጥሰት በሚፈጽሙት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ባለስልጣኑ የሀገሪቱን ህግ ባላከበሩና ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጭ በተንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ላይ ሲያደርግ የነበረው ምርመራ መጠናቀቁንና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

"ይህን ተከትሎ እርምጃ ይወሰዳል" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የሚወሰደው እርምጃ ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ህግና ስርዓትን አክብረው እንዲሰሩ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም