መንግስት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚወስዳቸው እርምጃዎችን የሚፈትሽ ጥብቅ አሰራር መዘርጋት አለበት

96

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ወጤታማነትን ሚፈትሽበት ጥብቅ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት የምጣኔ ሃብት ምሁራን ተናገሩ።

የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወቅታዊ ፈተና መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

አዲስ የተመሰረተው መንግስትም የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሰራቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል የሚወሰዱ እርምጃዎች በትክክል ውጤት ማምጣታቸው የሚፈተሽበት ጥብቅ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ንግድ ስራ ኮሌጅ የምጣኔ ሃብት መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ መንግስት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚወስዳቸው ተግባራት ሊኖሩት ይገባል ብለዋል።

የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመፍታት ጊዜ የሚወስዱ ጉዳዮች ቢኖሩም በአጭር ጊዜ መፍትሄ ወሳኝ የሆኑ የፍጆታ እቃዎች በተሻለ መንገድ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የሚረዱ አሰራሮችን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ይልቃል ዋሴ በበኩላቸው መንግስት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማስተካከል ቅድሚያ እሰጣለሁ ማለቱን በበጎ አንስተዋል።

የኑሮ ውድነት በፖሊሲና ስትራቴጂ ለመፍታት የሚወሰዱ እርምጃዎች ውጤት እንዲኖራቸው መነሻውን በጥናት መለየት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ሳትወድ በግድ የገባችበት ጦርነት ለኑሮ ውድነት አንደኛው ምክንያት መሆኑን በማንሳት፤ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ህብረተሰቡ ወደ ሰላማዊ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲገባ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዋጋ ንረቱ በጣም እየጎዳ ያለው ዝቅተኛና ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በመሆኑ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ የሚተገበሩ መመሪያዎችን የማስፈጸም አቅም እንዲጠናከር መክረዋል።

ጠንካራ የምጣኔ ሃብት፣ የፖለቲካ ስርአትና ማህበራዊ ተቋማትን መገንባት በረዥም ጊዜ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መፍትሄ እንደሚሆኑ የምጣኔ ሃብት መምህሩ ጠቁመዋል።

በዩኒቨርስቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሙኽዲን መሃመድ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ የአጭር ጊዜ መፍትሄ አድርጎ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ግልጽ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በማስቀመጥ ቁጥጥርን ማጠናከር፣ የምርት መሰረትንና አቅራቢዎችን ማስፋት የችግሩ መፍትሄ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት፣ ሰላምን ማስፈን ደግሞ በረዥም ጊዜ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የሚያገለግሉ ተግባራት መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

መንግስት በገበያ ስርአቱ ውስጥ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት የገበያ እንከኖችን ለመሸፈን እንደሚረዳ  ረዳት ፕሮፌሰር ሙኽዲን ጨምረው ገልጸዋል።

አዲስ የተመሰረው መንግስት ለሌብነት መስመር የማይከፍት ጠንካራ የምጣኔ ሃብት ስርአት መዘርጋት እንዳለበት ነው ምሁራኑ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም