አሸባሪው ህወሃትን በተባበረ ክንድ እስከመጨረሻው ለመደምሰስ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል

96

ጥቅምት 12/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃትን በተባበረ ክንድ እስከመጨረሻው ለመደምሰስ በሚደረገው ተጋድሎ ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ደጀንነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጢጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹም የአገር መከላከያ ሰራዊት ወራሪውን የሽብር ኃይል ለማጥፋት የሚያደርገውን ተጋድሎ በማገዝ ደጀንነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ማህበረሰቡ አሸባሪው ህወሃት የሚነዛውን የፈጠራ ወሬ በመቀበል አንዳንድ ግለሰቦች አካባቢያቸውን ለቀው ከመሄድ በመቆጠብ ለሰራዊቱ የሚያደርጉትን ደጀንነት እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

አሸባሪው ኃይል “ያልያዘውን ያዝኩ ያልተቆጣጠረውን ተቆጣጠርኩ” እያለ በሀሰተኛ ወሬ ህዝብን ለማወናበድ ሲጥር እንደሚስተዋልም ተናግረዋል።

ከሰሞኑም ወራሪው ኃይል “ደሴ ከተማን ተቆጣጥሪያለሁ” በማለት ነጭ ውሸቱን በማህበራዊ የትስስር ገጾች ሲያራግብ መስተዋሉን አንስተዋል።

ነገር ግን በደሴም ሆነ በጢጣ ከተሞች የሚታየው ህዝባዊ እንቅስቃሴ የሽብር ቡድኑ ከንቱ ምኞቱን እንደሚያወራ ማሳያ ነው።

የከተማዋ ወጣቶች የአገር መከላከያ ሰራዊት፣የአማራ ልዩ ኃይልና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች የአሸባሪውን ኃይል ለማጥፋት እያደረጉት ያለውን ተጋድሎ በማገዝ ደጀንነታቸውን አስመስክረዋል።

አሸባሪው ህወሃት ጢጣን ተሻግሮ ደሴን ተቆጣጥሪያለው ማለቱ “የተለመደ የበሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳ ነው” ብለዋል ነዋሪዎቹ።

የአገር ሰላም ያለመስዋዕትነት ሊረጋገጥ አይችልምና ጨፍጫፊው የአሸባሪው ህወሃት እስኪደመሰስ ድረስ ደጀንነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በጦርነት ቀጣና ያለው ማህበረሰብም ጠንካራ ስነ ልቦናን በመላበስ ከአካባቢው ሳይወጣ የሰራዊቱን ተጋድሎ ማገዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በቀጣይም የአሸባሪውን ህወሃት መቃብር በአማራ ምድር ለማድረግ በተባበረ ክንድ ሁለንተናዊ ትግሉ ህዝቡ እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል።