ኢትዮጵያ በታሪኳ የገጠማትን ፈተናዎች ሁሉ በድል የተወጣችው የሕዝቦቿ ውስጣዊ አንድነት ጠንካራ በመሆኑ ነው

80

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በታሪኳ የገጠማትን ፈተናዎች ሁሉ በድል የተወጣችው በሕዝቦቿ ውስጣዊ አንድነት ጥንካሬ እንደሆነ የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ወሰን ባዩ ገለጹ።

የአሁኑ ትውልድ እንደ ቀደምት አባቶቹ ሁሉ ተባብሮና አንድነቱን ጠብቆ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ማለፍ እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

እነዚሁ ሕዝቦች በየዘመኑ የገጠማቸውን ፈተናዎች ብዝሓ ማንነታቸው ሳይለያቸው በጋራ ሆነው አልፈዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ባህል ተመራማሪው ዶክተር ወሰን ባዩ፤ ”የኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነት ፈተናዎችን እንድታልፍ ማስቻሉ ታሪክ ይመሰክራል” ይላሉ።

እንደ ዶክተር ወሰን ገለጻ፤ኢትዮጵያውያን አድዋን የሚያክል ድል የተቀዳጁት፣የካራማራን ድል ያገኙት አንድነታቸው የጸና በመሆኑ ነው።

በአደዋ ጦርነት ወቅት ጣሊያናዊያን የጦር መሪዎች “ኢትዮጵውያን ይከፋፋላሉ፣ በአጭር ጊዜም ድል እናገኛለን ቢሉም ያ ሊሆን አልቻለም” በማለት ታሪክን ያጣቅሳሉ።

ይህም ሊሆን የቻለው ደግሞ”የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ በመቆሙና ሕዝቡም የተሳሰረ ማንነት ስላለው ነው” ይላሉ።

የኢትዮጵያውያንን የተሳሰረ አንድነት ምንም አይነት ፈተና ሊበግረው እንደማይችልም በተለያዩ ጊዜያት የተረጋገጠ ሀቅ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህ ወቅትም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ብሔርንና ኃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግጭቶች እንደሚስተዋሉ ጠቅሰዋል።

”እነዚህ ግጭቶች በምንም መልኩ የሕዝቡ ሊሆኑ አይችሉም” ያሉት ዶክተር ወሰን፤ግጭቶቹ ሌላ ተልዕኮ ያነገቡ አካላት የሚፈጥሯቸው መሆናቸውን ነው የሚናገሩት።

ይህን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ያለፈችበትን ሂደት መመልከት ብቻ በቂ መሆኑንም ነው የገለጹት።

“የአሁኑ ትውልድ እንደ ቀደምት አባቶቹ ሁሉ ተባብሮና አንድነቱን ጠብቆ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ማለፍ ይችላል” ብለዋል።

ይህ እውን እንዲሆንም ምሁራን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ከታሪክ እየተማሩና የተሳሳቱ ትርክቶችን እያረሙ አንድነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ዶክተር ወሰን አጽዕኖት ሰጥተዋል፡፡