የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በዘመቻ መስጠት ተጀመረ

82

ዲላ ፤ባህር ዳር፤ አሶሳ፤ነገሌ፤ መቱ ጥቅምት 12/2014 (ኢዜአ ) ህጻናትን የሚያጠቃው የልጅነት ልምሻ /ፖሊዮ/ በሽታን መከላከያ ክትባት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መስጠት ተጀመረ።

ለቀጣይ አራት ቀናት የሚካሄደው የክትባት ዘመቻ በጌዴኦ ዞን በዲላ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ በመገኘት በይፋ ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ  ዶክተር ደረጀ ዱጉማ  እንዳሉት፤ የፖሊዮን በሽታ ለመከላከል በሀገር ደረጃ አዲስ ለሚወለዱ ህጻናት ክትባት መስጠትና የበሽታ ቅኝት ስራዎችን ጨምሮ በተተገበሩ ዘረፈ ብዙ ስራዎች ለውጦች ተመዝግበዋል።

ሆኖም የልጅነት ልምሻ/ፖሊዮ/ መድሃኒት እጥረት ሳቢያ በሀገር ውስጥና አጎራባች ሀገራት የበሽታው ምልክት መታየቱን ጠቁመዋል።

በሽታውንም ባለበት ለመግታት በመደበኛ ከሚሰጠው ክትባት በተጨማሪ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ከ17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ለሚበልጡ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ክትባት ለመስጠት ዘመቻው መጀመሩን አስታውቀዋል።

የኮሮና መከላከያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በግብዓትና በሰው ሃይል በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው ህብረተሰቡ ልጆቹን በማስከተብ በሽታውን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

የህጻናትን የሞት ምጣኔ ለመቀነስ ክትባቱ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ናቸው።

በክልሉ ከ3 ሚሊዮን 60 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህጻናት ክትባቱን ለመስጠት 6 ሺህ 648 የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ወሰደው መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

ከዘመቻው በተጓዳኝ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ህጻናት የመለየት፣ የኮሮና ክትባትና ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎች እንደሚካሄዱም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የክትባት ዘመቻው ዛሬ በባህር ዳር ኤስ ኦ ኤስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲጀመር የክልሉ ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮራም አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ እንደገለጹት፤ በሽታው በምዕራብ ጎጃም ቡሬ ዙሪያ፣ በሰሜንና ደቡብ ወሎ ጉባ ላፍቶና አርጎባ ልዩ ወረዳ እንዲሁም በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ዳዋ ጨፋ ወረዳዎች ተከስቷል።

ይህን ለመከላከልም ከፀጥታ ስጋት ነፃ በመሆኑ አካባቢዎች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህፃናት ክትባቱን በዘመቻው እንዲወስዱ ይደረጋል ነው ያሉት።

ወረርሽኙ ተስፋፍቶ በህፃናት ላይ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ከዛሬ ጀምሮ ለአራት  ቀናት በሚሰጠው ክትባት ወላጆች ልጆቻቸውን በማስከተብ ሊተባበሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ክትባቱም በትምህርት ቤት፣ በጊዜያዊ መጠለያ ቦታዎችና ቤት ለቤት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከ5 ዓመት ዕድሜ በታች የሚገኙ ልጆች ክትባቱን እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

የባህር ዳር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስማማው ሞገስ በበኩላቸው የመጀመሪያው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ 55 ሺህ ለሚጠጉ ህፃናት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በክትባት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የሃይማኖት አባቶች  ህብረተሰቡ የፖሊዮ ወረርሽኝ በሽታ ለማጥፋት እየተደረገ ላለው ጥረት የጤና ባለሙያዎች እንዲተባበሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ነጻ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ94 ሺህ በላይ ህጻናት እንደሚከተቡ የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዋጮ ዋቡልቾ አስታውቀዋል።

ክትባቱን ከሚወስዱት ህጻናት መካከል ከ14 ሺህ በላይ የሚሆኑት በሸርቆሌ፣ ጾሬ እና ባምባሲ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የተለያዩ አፍሪካ ሃገራት ስደተኞች ልጆች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ጉጂ እና  ኢሉባቦር ዞኖች ከ444ሺህ ለሚበልጡ ህፃናት ተጠቃሚ የሚያደርግ የቤት ለቤት  ክትባት ዛሬ መስጠት መጀመሩን የየዞኖቹ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤቶች አስታውቀዋል።

የጉጂ ዞን ጤና ጥበቃ በጽህፈት ቤት የክትባት ባለሙያ አስተባባሪ አቶ መስፍን ካሳዬ እንዳሉት፤ ክትባቱን የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ተሰማርተዋል።

የፀጥታ ችግር ካለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በስተቀር በዞኑ በሁሉም ወረዳዎችና ገጠር ቀበሌዎች ይሰጣል ብለዋል።

በዚህም እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 261ሺህ 636  ህፃናት ክትባቱን እንደሚወስዱ አብራርተዋል።

በመቱ ከተማ የአብዲ ቦሪ ሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል በመገኘት የክትባት ዘመቻውን ያስጀመሩት ደግሞ የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።

በዚህ ወቅት የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መገርሳ ማሞ እንደገለጹት፤ በተጀመረው የክትባት ዘመቻ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ከ183 ሺህ በላይ ሕጻናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

በኢሉባቦርና ቡኖ በደሌ ዞኖች ዘመቻውን የሚያስተባብሩት የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ መንበሩ ጌታቸው እንዳሉት በሀገሪቱ ላለፉት አርባ ዓመታት ያህል በመደበኛነት ሲሰጥ በነበረው የፖሊዮ ክትባት በሽታው ወደመጥፋት ተቃርቦ ነበር።

ክትባቱ በመደበኛነት መሰጠቱ እየቀነሰ በመምጣቱ ተመልሶ የመስፋፋት አዝማሚያ ተስተውሎበታል ብለዋል፡፡

ሕጻናት በዚህ በሽታ ለአካል ጉዳትና ህልፈት እንዳይዳረጉ ለመከላከል የሚከናወነው ስራ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም መረባረብ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የልጅነት ልምሻ/ፖሊዮ/ በሽታ መከላከያ  ክትባት ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት በመላው ሀገሪቱ  ጤና ተቋማትና ቤት ለቤት  እንደሚሰጥ ታውቋል።