የኮሙዩኒኬሽን ተቋማት ለሳይበር ደህንነት ምን ያህል ትኩረት ሰጥተዋል?

444

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2014(ኢዜአ) የኮሙዩኒኬሽን ተቋማት ለሳይበር ደህንነት ምን ያህል ትኩረት ሰጥተዋል?

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የሳይበር ደህንነት ወርን አስመልክቶ ከፌዴራልና ክልል ኮሚዩኒኬሽንና ከፖሊስ ተቋማት የተውጣጡ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች የተቋማቱ የመረጃ ፍሰት ከሳይበር ደህንነት ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ በኃላፊነትና በጥንቃቄ እየሰሩ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የማህበራዊ ሚዲያ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ መኮንን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ ባለሙያዎች በሳይበር ድህንነት በቂ ግንዛቤ ከሌላቸው ለመረጃ መንታፊዎች እንደሚጋለጡ ተናግረዋል፡፡

በመረጃ መንታፊዎች ከተጋለጠ ደግሞ ከፍተኛ አገራዊ ኪሳራ ስለሚደርስ በኮሙዩኒኬሽን ተቋማት ማህበራዊ ሚዲያ ይህን ታሳቢ ያደረገ ጥንቃቄ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በዚህም በማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃን አያያዝ፣ አደረጃጀት ላይ በጥንቃቄና በኃላፊነት እየሰራን ነው ብለዋል።

በሐረሪ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሸን ቢሮ ባለሙያው አቶ ዲኒር የሱፍ በመንግስት መረጃ ፍሰት ከፍተኛ ሚና ያላቸው የኮሙዩኒኬሽን ተቋማት እየጨመረ በመጣው የሳይበር ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ተቋማቸው ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ በማይሆንባቸው አግባብ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርጉበት አሰራር ላይ ትኩረት ስለማድረጋቸው አንስተዋል።

በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የማህበራዊ ሚዲያና የህትመት ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር የትናየት ጥበቡ እንደሚሉት፤በደቂቃዎች ውስጥ ብዙሃንን ተደራሽ የሚያደርገው ማህበራዊ ሚዲያ አስተዳደር ጥንቃቄ ይሻል።

ጥንቃቄ የጎደለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ደግሞ ከተቋማት ባለፈ ሀገርን አደጋ ላይ እንደሚጥል ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ስነ ምግባርና ኃላፊነትን ከግምት ውስጥ ያስገባ አጠቃቀም ሊተገበር ይገባል ነው ያሉት።

አሸባሪው የህወሃት ኃይል እያደረሰ ባለው ጥቃት ጋር ተያይዞ ፈጣን እና ትክክለኛ መረጃ ከማድረስ አኳያ የክልሉ ፖሊስ ማህበራዊ ሚዲያ ዘርፍ በትጋት እየሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ህብረተሰቡን ስለሚያደናግር ህብረተሰቡ መረጃዎችን ከታማኝ ምንጮች ብቻ መውሰድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ቢሮ የኢንፎርሜሸን ኮሙዩኒኬሸን ክፍል ሃላፊው አቶ እንዳለ ታከለ በበኩላቸው የኮሙዩኒኬሽን ቢሮው የክልሉ መረጃ ፍሰት ዋና ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።

ከመረጃ ማስተላለፊያ ዘዴዎች አንዱ በሆነው ማህበራዊ ሚዲያ በመረጃዎች ፍሰት ላይ ዕውቅና በተሰጣቸው የበይነ መረብ አማራጮች ይዘት አስተዳድር ባለሙያዎች ብቻ ይመራል ብለዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት በቢሮው የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጽ ላይ የሳይበር ጥቃት አለመድረሱን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ከወዲሁ የሳይበር ጥቃትን ከግምት ውስጥ ባስገባ አግባብ በጥንቃቄና በሃላፊነት እየሰሩ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ድንበር ተሻጋሪ የሳይበር ጥቃት የወቅቱ ቁልፍ ዓለም አቀፋዊ ስጋት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንተነህ ተስፋዬ ናቸው።

የሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከሳይበር ቴክኖሎጂ ጋር የተጣመረ መሆኑን ጠቁመው፤ የሳይበር ጥቃት ጉዳይ የአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚነካ በመሆኑ እጅግ የላቀ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

የዓለማችን የወደፊት ዐውደ ውጊያዎች በሳይበር መራሽ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም የሳይበር ደህንነት ዓለም አቀፍ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በኢትዮጵያም የሳይበር ጥቃት በተወሰኑ መገናኛ ብዙሃንን ላይ መከሰቱን አስታውሰው፤ በጉዳዩ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል በጋራ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በፈረንጆቹ 2020 ዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጸመ የሳይበር ጥቃት ዓለማችንን 2 ነጥብ 5 ትርሊየን ዶላር ያሳጣ ሲሆን፤ በ2025 ደግሞ 6 ትርሊየን ዶላር እንደሚያሳጣ ይገመታል።

በመገናኛ ብዙሃን ረገድ ብቻ በተደረገ ጥናት ደግሞ በ2020 መገናኛ ብዙሃን ማግኘት የነበረባቸውን 90 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ በሳይበር ጥቃት ሳቢያ እንዲያጡ ሆነዋል።