ለውጭ ገበያና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚቀርብ አኩሪ አትር እየተሰበሰበ ነው

117

መተማ (ኢዜአ) ጥቅምት 12/2014 በምዕራብ ጎንደር ዞን ለውጭ ገበያና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ለማቅረብ በ28 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ የለማ አኩሪ አተር እየተሰበሰበ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ ከሰሊጥ በተጨማሪ ለአኩሪ አተር ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

አርሶ አደሩና በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ለአካባቢው የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑና ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ሰብሎችን በስፋት እያለሙ መሆኑን ገልፀዋል።

የአኩሪ አተር ልማትን ለማስፋፋት በተሰጠው ትኩረት በመኽር ወቅት 28 ሺህ 300 ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ለምቶ በአሁኑ ወቅት መሰብሰበ መጀመሩንም ተናግረዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ 10 ሺህ ሄክታር የሚጠጋን መሬት ያለሙት 216 ባለሃብቶች ሲሆኑ ቀሪው መሬት በአርሶ አደሮች ተሳትፎ የለማ ነው።

በአጠቃላይ በአኩሪ አተር ከለማው መሬት 590 ሺህ ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ትብሎ እንደሚጠበቅና ለሚሰበሰበው ምርትም የገበያ ትስስር የተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የሙሉዓለም ምልምሌ የእርሻ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ጥጋቡ በበኩላቸው በመኽሩ እርሻ 240 ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር መልማቱን ጠቅሰዋል።

የአኩሪ አተር ልማቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው ይህም የልማቱን ተሳታፊዎች ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ካላቸው 10 ሄክታር መሬት 2 ሄክታሩን በአኩሪ አተር ማልማታቸውን የገለፁት ደግሞ በዞኑ የቋራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጌትነት አበየ ናቸው።

“ለምርታችን የገበያ ትስስር በመፈጠሩና የሰብሉ አያያዝም ጥሩ በመሆኑ ደስተኛ ነን” ያሉት አርሶ አደሩ፣ በቀጣይም አኩሪ አተር በስፋት ለማምረት ማቀዳቸውን ገልፀዋል፡፡

በዞኑ በመኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው 370 ሺህ ሄክታር መሬት 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም የመምሪያው መረጃ ያመለክታል።