ዞኑ ተፈናቃይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ጀመረ

88

ደብረ ማርቆስ፤ ጥቅምት 12/2014 ዓ/ም ( ኢዜአ)፡ የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ የህወሃት የሽብር ቡድን ጦርነት በከፈተባቸው አካባቢዎች ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ 390 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ስለሺ ተመስገን ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ካደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት በተጨማሪ የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ህጻናትን ከትምህርት ገበታቸው እንዲነጠሉ አድርጓል።

"በዚህም ወገን ለወገን ደራሽነቱን ለማሳየት እና ክፉ ቀንን ተባብሮና ተደጋግፎ ለማለፍ ተማሪዎችን ከበጎ ፈቃደኛ ግልሰቦች ጋር በማገናኘት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ ይገኛል" ብለዋል።

ተማሪዎቹ በጎንቻ፣ አነደድ፣ ሁለት እጁ እነሴ፣ሞጣ፣ ማቻከል እና ሌሎችም ወረዳዎች በሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ አመልክተዋል።

ለመማር ማስተማር አጋዥ የሆኑ የትምህርት ቁሳቁሶችና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ተሟልቶላቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተጨማሪ ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር የሚፈልጉ በጎ ፈቃደኞች ተመዝግበው ተማሪዎችን እየተጠባበቁ እንደሆነም ሃላፊው ገልፀዋል።

የሞጣ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ማህሪ ባወቀ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ከ30 በላይ ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ  ከስነ-ልቦና ግንባታ ጀምሮ  አስፈላጊው ድጋፍ እና እገዛ  እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ከሰቆጣ ተፈናቅሎ በሁለት እጁ እነብሴ ወረዳ እነብሴ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን መከታተል የጀመረው ተማሪ ዳረንጎት ቆየ በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ በመፈናቀሉ  ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆኖ መቆየቱን አስታውሷል።

''ቡድኑ የ11ኛ ክፍል ትምህርቴን በማቋረጥ እንድሰደድና ተስፋ እንድቆርጥ ቢያደርገኝም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አለሁ የሚል ወገን በማግኘቴ ተስፋዬ መልሶ ለምልሟል'' ብሏል።

የህወሓት የሽብር ቡድን የፈፀመው ግፍ  መቼም ቢሆን ከህሌናው የማይጠፋ ጥቁር ጠባሳ የጣለበት መሆኑን ጠቅሶ፤ የተሰጠውን እድል በመጠቀም በትምህርቱ ውጤታማ ለመሆን መዘጋጀቱን ተናግሯል።

ከሰሜን ወሎ ዞን ጋሸና የመጣው ተማሪ ግርማ የኔሰው በበኩሉ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ትምህርት ቤታቸውን በመዝረፍና በማፈራረስ በደል መፈጸሙን ጠቁሟል።

መልሶ ለመማር በተፈጠረለት እድል  በሞጣ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ትምህርቱን እየተከታተለ መሆኑን አመልክቷል።

አስፈላጊው የመማሪያ ቁሳቁስ እንደተሟላለት የጠቀሰው ተማሪ ግርማ፤ ተቀብለው እንደልጆቻቸው እየተንከባከቡት እያስተማሩት ላሉት ቤተሰቦች  ምስጋና አቅርቧል።

ዞኑ ህወሓት በከፈተው ጦርነት በአካባቢያቸው መማር ያልቻሉ ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎችን  ተቀብሎ ለማስተማር እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም