የትግራይ ህዝብ እንደሌላ ኢትዮጵያዊ ሀገሩን የመገንባት አኩሪ ታሪኩን በመጠበቅ አሸባሪውን ህወሃት ሊያወግዝ ይገባል

349

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 12/2014(ኢዜአ)የትግራይ ህዝብ እንደሌላ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሀገሩን የመገንባት አኩሪ ታሪኩን በመጠበቅ የአሸባሪውን የህወሃት ቡድን እኩይ ተግባር ሊያወግዘው እንደሚገባ ተመለከተ።
የብልጽግና ፓርቲ  የትግራይ ክልል ጽህፈት ቤት አመራሮች በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ አወያይተዋል።

በጽህፈት ቤቱ የድርጅት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ገብረፃዲቅ ገብርመድን በውይይት መድረኩ እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሓት  ቡድን ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ በህዝብና  ሀገር ላይ  የጥፋት ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል።

የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው ሴራ ሳይታለል እንደሌላ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሀገሩን በመገንባት ላይ ያለውን አኩሪ ታሪክ መጠበቅ እንዳለበት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ስትኖር ብቻ ነው የትግራይ ህዝብ ህልውና የሚኖረው፤ ችግሮች ካሉ በውይይት መፍታት ይቻላል ነው ያሉት ኃላፊው።

አሁን ላይ  በሽብር ቡድኑ  ህፃናትና ነፍሰ ጡር እናቶች ሳይቀሩ የጦርነት ሰለባ እየሆኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ህዝቡ የህወሓት የሽብር ቡድንን እኩይ ሴራ በመገንዘብ  የጥፋት ድርጊቱን ሊወግዝ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የሰሜን ዕዝን በክህደት የጨፈጨፈው ዘራፊና ማፈያ የህወሓት ቡድን  የትግራይ ህዝብን እንደማይወክል  አውስተዋል።

አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነት አውዳሚ መሆኑን ቢገነዘብም  የሀገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅ ሲባል ቡድኑን የማስወገዱ ስራ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል የመንግስት ተጠሪ አቶ ላከደር ላክባክ በመድረኩ  እንደተናገሩት የህወሓት የሽብር ቡድን የህዝቦችን አንድነትና እኩልነት የማይቀበል የአሽብር ቡድን ነው።

ለዚህም ማሳያው ባለፈው 27 ዓመታት ጋምቤላ ጨምሮ አራቱ ክልሎች አጋር ተብለው ከለውጡ ወዲህ ፓርቲያቸው ሲዋሃድ  አፈንግጦ መውጣቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ወንደሙ ሃየሎም በሰጡት አስተያየት፤ ሀገር እናፈርሳለን የሚለው አስተሳሰብ ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

አሁንም ቢሆን ሀገር ለማፍረስ የተቃጠውን ችግር ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።