አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሽንፈቱን በጥፋት ስራ ለመሸፈን ያቀዳቸውን ሴራዎች ማክሸፍ ይገባል

97

ጥቅምት 12/2014(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ደሴ ከተማን ኢላማ አድርጎ ያቀዳቸውን በርካታ የጥፋት ተግባራትን በመረዳት ሃገርን ለመበታተን አቅዶ የተነሳውን የጥፋት ሃይል ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባው መንግስት ጥሪ አቀረበ።

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ አሸባሪው ቡድን በሁሉም ግንባሮች በመከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ለህልውናቸው በተሰለፉት የክልሉ ወጣቶች የሚደርስበት ከባድ ኪሳራ ሩቅ አያስኬደውም።

ቡድኑ በደሴ ከተማ ላይ ያቀደው ጥፋትም ይህንኑ ሽንፈቱን በጥፋት ስራ ለመሸፈን ማቀዱን ያሳያል ያለው መግለጫው፤ ህብረተሰቡም የሽብር ቡድኑን እኩይ አላማና እቅድ በመረዳት ሃገርን ለመበታተን አቅዶ የተነሳውን የጥፋት ሃይል ሴራ ማክሸፍ ይገባዋል ብሏል። ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል። --------------------------

አሸባሪው የህወሃት ጁንታ ቡድን ደሴ ከተማን ኢላማው አድርጎ የሚያቅዳቸው በርካታ የጥፋት ስራዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው።በሁሉም ግንባሮች በጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ በአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ለህልውናቸው በተሰለፉት የክልሉ ወጣቶች የሚደርስበት ከባድ ኪሳራ ሩቅ እንደማያስኬደው ግልጽ ሆኗል።

የደሴ ከተማ ላይ ያቀደው ጥፋትም ይህንኑ ሽንፈቱን በጥፋት ስራ ለመሸፈን ማቀዱን ያሳያል። ህብረተሰቡም የዚህን ሽብር ቡድን እኩይ አላማና እቅድ በመረዳት ሃገርን ለመበታተን አቅዶ የተነሳውን የጥፋት ሃይል ሴራ ማክሸፍ ይገባዋል።

የሽንፈት ገፈትን እየቀመሰ የሚገኘው የሽብርተኛው ቡድን በደሴ ብዙ ሰራዊት ሊኖር ይችላል በሚል በተጨማሪም ፋኖ የከተማ የውጊያ ስልትን ለማካሄድ ሊዘጋጅ ይችላል የሚል ግምትን በማሳደር ሰርጎ ገቦችን በመጠቀም በከተማዋ የመብራት መስመሮችን ለማቋረጥ እና በደሴ የሚገኘው የፀጥታ ሃይል ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለማሳደር ማቀዱን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።

በከተማዋ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ የክልሉ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ከመረጃ እንዲርቅ ማድረግንም በእቅዱ ይዟል። ሃሰተኛ መረጃዎችንና ምስሎችን በስፋት በማሰራጨትም የሰራዊቱንና አጠቃላይ የፀጥታ ሃይሉን ሞራል ለማዳከም ያስችሉኛል በሚል የያዛቸው እቅዶች መኖራቸው ተደርሶበታል።

ይህ የጥፋት ቡድን ሃገርን ማሸበር ዋና አላማው መሆኑን የሚያሳይ ነው። የአማራ ክልል ህዝብና መላው ኢትዮጵያውያን የሽብር ቡድኑ ህወሃት ያቀዳቸውን የማወናበጃና የህብረተሰቡን ኢኮኖሚና ማህበራዊ ተግባራት የማወክ እንቅስቃሴን ቀድሞ በመረዳት ሰርጎ ገቦችን በማጋለጥና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ እንደስካሁኑ ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት መልእክት ያስተላልፋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም