በነቀምቴ ከተማ በ63 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የመሠረተ ልማት ግንባታ ተከናወነ

77
ነቀምቴ ነሃሴ12/2010 የነቀምቴ ከተማን ልማትና እድገት ለማፋጠን ከ63 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን የከተማው አስተዳደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የመሰረተ ልማት ስራ ሂደት ባለቤት ኢንጅነር ተፈሪ ተስፋዬ እንደገለጹት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከተከናወኑት የመሠረተ ልማት ኘሮጀክቶች መካከል የመንገድ ግንባታ ዋነኛው ነው። በቅርቡ ተጠናቀው ለአገልግሎት ከበቁት መካከል የ6 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የኮብል ድንጋይ ንጣፍና 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መውረጃ ቦይ ግንባታ ይገኝበታል። እንዲሁም ሁለት አነስተኛ ድልድይና 7 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ዳር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን ጠቅሰዋል። ከተማዋን ጽዱና ማራኪ ለማድረግም የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት መካሄዱን ጠቁመው የኢንተርፕራይዞችን የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ችግር ለማቃለል የገበያ ማዕከላት ተገንብተዋል፡፡ ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የልማት ፕሮጀክቶች ከ24 ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በግንባታ ሂደትም 780 የከተማዋና አካባቢው ወጣቶች በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በከተማው የ04 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገለታ ነጋሳ በሰጡት አስተያየት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገነቡት መሰረተ ልማቶች በጥራትም ሆነ በስፋት ከዓምናው የተሻሉ ናቸው። በተለይ የኮብል ድንጋይ ንጣፍ መንገዱ ለከተማዋ ውበት ከመስጠቱም ባለፈ ነዋሪው በበጋና ክረምት ያለምንም ችግር ለመንቀሳቀስ እያስቻሉት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በከተማው በማህበር ተደራጅተው በኮብል ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራ ላይ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል ወጣት ጋድሴ ዓለሙ  በሰጠችው አስተያየት በከተማው በተከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆኗን ገልፃለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም