መንገዱን በመሳት መኖሪያ ቤት ውስጥ የገባው ተሽከርካሪ የዘጠኝ ሰዎችን ህይወት አጠፋ

79

ጭሮ ሚያዝያ 22/2010 በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሚኤሶ ወረዳ ዛሬ ጠዋት መንገዱን ስቶ መኖሪያ ቤት ውስጥ የገባው የጭነት ተሽከርካሪ ተኝተው የነበሩ  የዘጠኝ  ሰዎች ህይወት ማጥፋቱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

 የሚኤሶ ወረዳ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ኃይለማርያም ጥበቡ እንደገለፁት አደጋውን ያደረሰው ከጭሮ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሮ ኮድ 3 -27193አ.አ. የሆነ የጭነት ተሽከርካሪ ነው፡፡ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈው በእንቅልፍ ላይ የነበሩ ዝምድና ያላቸውና የሁለት  ቤተሰብ አባላት ናቸው፡፡ በሚኤሶ ወረዳ ሁሴ በተባለ ቀበሌ ማህበር ዛሬ ጠዋት 12 ሰዓት አካባቢ በደረሰው በዚሁ አደጋ ህይወታቸው ካለፈው መካከል  የሁለቱም ቤተሰብ  እማወራዎች ሲገኙበት አባወራዎቹ ግን ተርፈዋል። በአደጋው  ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች በተጨማሪ አሽከርካሪውን ጨምሮ በ5 ሰዎች ላይ  ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱንም ምክትል ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል ። ዕቃ የጫነው ተሽከርካሪ መንገዱን ስቶ መኖሪያ ቤት ውስጥ ገብቶ የተገለበጠበትና የከፋ አደጋ ያደረሰበት መንስኤ እየተጣራ ነው ተብሏል ። ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰበት አሽከርካሪም በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን ፖሊስ አያይዞ ገልጿል ። የሟቾቹ የቀብር ስነስርዓት ዛሬውኑ የተፈፀመ ሲሆን ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በጭሮ ሪፈራል ሆስፒታል በህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ። አሽከርካሪዎች የወገኖቻቸውን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም ህይወት ጭምር ከከፋ አደጋ ለመታደግ ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው እንዲያሽከረክሩ ረዳት ኢንስፔክተሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም