በአባይ ጉዳይ ለተፋሰሱ አገሮች የሚጠቅመው በትብብርና በመተጋገዝ መስራት ብቻ ነው

67

ጥቅምት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአባይ ጉዳይ ለተፋሰሱ አገሮች የሚጠቅመው "በትብብርና በመተጋገዝ መስራት ብቻ ነው" ሲሉ የፖለቲካ ተንታኙ መሀመድ አል አሩስ ገለጹ።

የፖለቲካ ተንታኙ መሀመድ አል አሩስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የአባይ ጉዳይ በትብብርና በመተጋጋዝ የሚሰራ ነው።

በአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ተባብረው በመስራት ፍትሃዊ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ነው ያመለከቱት።

ነገር ግን ግብጽ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ኢትዮጵያ እንዳትገነባ በተለያየ መልኩ ስትጥር እንደነበረ አስታውሰዋል።

"ግብፅ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ኢትዮጵያ  ደካማና ያልተረጋጋች ሀገር ሆና እንድትቀጥል  ፍላጎቷ  አላት" ብለዋል፡፡

የግብፅ ባለስልጣናት ከድሮ ጀምሮ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና ምስራቅ አፍሪካን በማዳከም በቀጠናው የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ለማሟላት ሲንቀሳቀሱ እንደኖሩም አስታውሰዋል።

ህዳሴ ግድብ እንዳይገነባ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ግፊት ግድቡ በቀጣናው ላይ ጉዳትና አለመረጋጋት ያደርሳል ብለው በማሰብ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

የግብጾች ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያ ከበለጸገችና ከለማች፣ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ዘርፍ በአፍሪካ ኃያል ትሆናለች ከሚል ስጋት የመነጨ መሆኑንም አስረድተዋል።

ያም ቢሆን "ኢትዮጵያ የግብፅን መገዳደርና ጣልቃ ገብነት በመታገል በሯሷ ሃብት የመበልጸግ መብቷን ማረጋገጥ አለባት" ብለዋል፡፡

የግብፅ መንግስት አካሄድ በአጠቃላይ ለቀጠናው የማይጠቅምና ግብፅ በአለም አቀፉ የፖለቲካ መደላድል ውስጥ ያላትን ተቀባይነት ገደል የሚከት መሆኑንም ተናግረዋል።

ለሶስቱ የተፋሰሱ አገሮች የሚጠቅመው ጉዳይ "በትብብርና በመተጋገዝ መስራት ብቻ ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ደጋግማ እንደምትገልጸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉዳት አያደርስም፡፡

በተለይም ግብፅ ግን ጉዳዩን ፖለቲካዊና አለም አቀፋዊ የክርክር ምንጭ በማድረግ ግንባታውን ለማስተጓጎል ያለ እረፍት እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

ከ86 በመቶ በላይ የአባይ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የምትገነባው በጨለማ ውስጥ እየኖረ ካለው በርካታ ህዝቧ ጥቂቱንም ቢሆን ብርሃን እንዲያገኝ ለማድረግ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም