ማህበሩ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ሙያዊ ኃላፊነቱን እየተወጣሁ ነው አለ

98

አርባ ምንጭ ፤ጥቅምት 11/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሙያዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር 34ኛው ጉባዔ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተጀምራል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ በጉባዔው ላይ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ በሀገሪቱ  ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት እያገዘ ነው።

መንግሥት የትምህርት ጥራት ችግሮች ለመፍታት እያዘጋጀ ላለው ፍኖተ ካርታ ውጤታማነት ግብዓት የሚሆኑ ስምንት ጥናታዊ ጽሁፎች መሰናዳታቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህም ብቃት  ያላቸው መምህራን ለማበራከት እንደሚያስችል የተናገሩት ዶክተር ዮሐንስ፤

ጥናታዊ  ጽሑፎቹ የትምህርት ጥራት ለመጠበቅ፣  የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች ሚና ላይ ያተኮሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ማህበሩ የመምህራንን መብት ከማስከበር ባለፈ በልማትና በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡

በተለይም አፍሪካን በመወከል የቦርድ አባል በሆኑበት የዓለም መምህራን ማህበር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ከአሸባሪው ህወሃት ጋር በተያያዘ ጉዳዮች ”የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን አቋም ማንፀባረቃቸውን  አስታውቀዋል።

ማህበሩ ከትምህርት ጥራት ባለፈ የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሃዊነትና ብቃት ላይ ችግር ፈቺ ጥናት ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የማህበሩ ስልጠናና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ኃይሌ ናቸው፡፡

የትምህርት ባለሙያዎችን በማስተባበር ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም  ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጥናፉ አስፋው በበኩላቸው ፤ ቢሮው ለመምህራን የዝውውርና የደረጃ ዕድገት መመሪያ በማዘጋጀት ጎታች አሠራሮችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየፈታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባዔ የ2013 በጀት ዓመት ክንውን ሪፖርትና የ2014 ዕቅድ ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከ600ሺህ በላይ አባላት ያሉት አንጋፋ የሙያ ማህበር ነው።