ተስፋን የሰነቁ ልቦች

76

ወይዘሮ ዜናዊት አስተካክለው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆኑ፤ የሁለት ዓመት ህጻን ልጅ አላቸው።

ልጃቸው በጸሎት ገዛኸኝ ገና የስድስት ወር ጨቅላ ህጻን እያለች ነበር የምግብ ፍላጎት ማጣትና አለመርጋት፣ የክብደት መቀነስ፣ የፊትና የሰውነት መገርጣት፣ መነጫነጭና እንቅልፍ ማጣት በተደጋጋሚ እንደሚከሰትባት ወላጆቿ የተገነዘቡት፡፡

ይህንንም ተከትሎም የህጻኗ ወላጆች በተደጋጋሚ ወደ ጤና ተቋማት ቢወስዷትም ከእለት ተለት ህመሟ እየተባባሰ ሄደ፡፡

በዚህም ህጿናን ለጠቅላላ ምርመራ ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ይዘዋት በሄዱበት ወቅት ነበር የልብ ህመምተኛ መሆኗን ያወቁት።

ህጻኗ ገና በጭቅላ እድሜ ላይ ያለች ከመሆኗ ባሻገር ህመሟ እየበረታ መምጣቱ ደግሞ በተለይ ለወላጆቿ እጅግ አስደንጋጭ እንደነበርም እናቷ ወይዘሮ ዜናዊት ይናገራሉ፡፡

በሆስፒታሉ እንደ ህጻን በጸሎት የልብ ህመም ያጋጠማቸው በርካታ ህሙማን በመኖራቸው ወረፋ መጠበቁ ደግሞ ሌላኛው ፈተና ነበር፤ ለህክምናው የሚያስፈልገው ወጪም እንዲሁ፡፡

ይሁን እንጂ በሆስፒታሉ የሚገኘው የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ለህጻን በጸሎት ህክምና የሚያስፈልገውን ከ100 ሺህ ብር በላይ ወጪ ሸፍኖ የተሳካ የቀዶ ህክምና አድርጎላታል።

የቀዶ ጥገና ህክምናው የህጻን በጸሎትን ጤና እና ደስታ እንደመለሰው የገለጹት እናቷ፤ "ይህም ለቤተሰቡ እፎይታን የፈጠረ ነው" ብለዋል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል መንዝ መሃል ሜዳ የጌራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አሰገደች ከበደ እናቷን በሞት ያጣችውንና የሚያሳድጓት የስምንት ዓመት ታዳጊ መቅደስ ሹመት ባጋጠማት የልብ ህመም ሳቢያ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ወረፋ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ታዳጊዋ ህክምናዋን የምትከታተለው ካለችበት አካባቢ ወደ አዲስ አበባ በመመላለስ መሆኑ ደግሞ "ካለብን የኑሮ ጫና አኳያ ችግሩን አስከፊ አድርጎብናል" ብለዋል፡፡

ታዳጊዋ ባጋጠማት ህመም ምክንያት ትምህርቷን መከታተል እንዳልቻለችም ነው የተናገሩት፡፡

ወረፋዋ ደርሶ ህክምናዋን ታገኛለች የሚል ተስፋ የሰነቁ ሲሆን፤ እንደ እኩዮቿ ደስተኛ የምትሆንበት፣ የምትቦርቅበት እንዲሁም ትምህርቷን የምትቀጥልበት ቀን ቅርብ ይሆናል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አርቲስት መሰረት መብራቴ በበኩሏ በልብ ህመም የሚሰቃዩ በርካታ ህጻናት በማዕከሉ እንዳሉ ተናግራለች፡፡

ይህንን በመገንዘብ ከማዕከሉ የጤና ባለሙያዎችና ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጻለች፡፡

በዚህም በአሜሪካን አገር በተለያዩ ከተሞች በመዘዋወር ለህጻናቱ መታከሚያ የሚሆን ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ በማከናወን ስድስት ሚሊዬን ብር ማግኘት መቻሉን ጠቅሳለች።

በአሜሪካ ለገቢ ማሰባሰብ በተዘዋወረችባቸው ከተሞች ሁሉ ቅን አሳቢና ቅን ልቦች ላደረጉት ድጋፍና ትብብርም ምስጋና አቅርባለች።

ማዕከሉ አሁን ባለው የፋይናንስ አቅም በሳምንት ለአስር ህጻናት ህክምና እያደረገ ቢገኝም ህክምናውን ከሚጠባበቁ ህጻናት ቁጥር አንጻር አነስተኛ ነው ያሉት ደግሞ የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሳምሶን አደራ ናቸው፡፡

በዚህም የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን በሁለት እጥፍ ለመጨመር እቅድ መያዙን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በአርቲስቷ ጥረት የተሰበሰበው ብር በማዕከሉ ለልብ ቀዶ ህክምና ወረፋ የሚጠባበቁ በርካታ ህጻናትን  እንደሚታደግም ተናግረዋል፡፡

ሌሎች አካላት የአርቲስት መሰረት መብራቴን አረአያ በመከተል ህጻናቱን እንዲያግዙም የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሳምሶን አደራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል በዶክተር በላይ አበጋዝ መስራችነት በ1981 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ ባለፉት 32 ዓመታት ከ9 ሺህ 500 በላይ ህጻናትን ወደ ውጭ በመላክ ህክምና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ባስገነባው ማዕከል የልብ ቀዶ ህክምና በነጻ በመስጠት ላይ የሚገኝ የተራድኦ ድርጅት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም