አካል ጉዳተኞች ለተፈናቀሉና ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ በማድረግ ሚናቸውን እየተወጡ ነው

74

ባህርዳር፣ ጥቅምት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) አባላቱ ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ በማድረግ ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ፈዴሬሽኑ ከባህርዳር ከተማ የአካል ጉዳተኞች ማህበር ጋር በመተባበር የዳቦ ዱቄትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ፍሬሰላም ዘገየ በድጋፍ ርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ፌዴሬሽኑ ከአባላቱ ባሰባሰበው 108 ሺህ ብር ወጭ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞች ሰርተው ከሚያገኙት ገንዘብ ቀንሰው ለተፈናቃዮች በመደገፍ ወገናዊ ሚናቸውን በተግባር ማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል።

አባላቱ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ በማድረግ ደጀን መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

አባላቱ የደም ልገሳና ተጨማሪ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

ደም ሲለግስ ያገኘነው ወጣት ቀፀላ መንግስቱ ለኢዜአ እንደገለፀው ሃገርን ከብተና ለማዳን ለሚፋለሙ የሰራዊት አባላት ደም መለገስ ሀገራዊ ግዴታን መወጣት ማለት ነው።

"የህልውና ዘመቻ ሲባል ሁሉም ግንባር ላይ መገኘት ብቻ አይደለም "ያለው ወጣት ቀፀላ፤ መዋጋት የማይችሉ በስንቅና በቁሳቁስ ድጋፍ በመሳተፍ የደጀንነት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁሟል።

ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ደም በመለገስና የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጧል።

ከዚህ ቀደም የአንድ ወር ደመወዛቸውን ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሊዲያ አስማማው፤ "ዛሬም ከባልደረቦቼ ጋር በመሆን በግንባር ተሰልፈው ለሚፋለሙ የጸጥታ አካላት ደም በመለገስ ሚናዬን እየተወጣሁ ነው" ብለዋል።

በአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን የህዝብ ግኑኙነት ሃላፊ አቶ እያሱ መስፍን "ድጋፉን በፍትሃዊነት ለሚመለከታቸው ተፈናቃዮች ለማድረስ ይሰራል" ብለዋል።

የክልሉ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽንና የባህርዳር አካል ጉዳተኞች ማህበር ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም