በአዲስ አበባ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት ሊሰጥ ነው

67

ጥቅምት 11/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ እድሚያቸው ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህጻናት ከነገ ጀምሮ የፖሊዮ ክትባት ሊሰጥ መሆኑን የከተማዋ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በጤና ቢሮው የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት ዳይሬክተር ቤተልሔም ታየ፤ የክትባት አሰጣጡን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በመጀመሪያው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እድሚያቸው ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ከ555 ሺህ በላይ ህፃናት ይሰጣል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከታህሳስ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ ዳሰሳ የፖሊዮ በሽታ አምጭ ተህዋሲያን መኖሩ ታውቋል ነው ያሉት።

በመሆኑም የመጀመሪያው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከነገ ጥቅምት 12 አስከ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ቤት ለቤት የሚሰጥ መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋለ።

ክትባቱን ቤት ለቤት የሚሰጡት የጤና ባለሙያዎች ለኮቪድ መከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው መሆኑን ጠቅሰው ወላጆችም ልጆቻቸውን በተጠቀሱት ቀናት ማስከተብ አለባቸው ብለዋል።

የሁለተኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከአንድ ወር በኋላ የሚሰጥ መሆኑም ታውቋል፡፡

ፖሊዮ ተላላፊ በሽታ ሲሆን በተለይም ከ1 እስከ 5 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት በብዛት ያጠቃል፡፡

የፖሊዮ የመጀመሪያ ደረጃ ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ማስታወክ እና የአካል ክፍሎች ላይ ህመም የሚያስከትል መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም