በባሌ ዞን አዲስ የተገነቡ 105 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር ጀመሩ

69

ጎባ ጥቅምት 10/2014 (ኢዜአ) በባሌ ዞን በመንግስት በጀትና በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ 105 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር መጀመራቸውን ዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
 የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ከበደ ለኢዜአ  እንደገለጹት በተያዘው 2014 የትምህርት ዘመን ስራ ከጀመሩ አዲስ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ ግንባታቸው የተጠናቀቀ 311 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ።

ትምህርት ቤቶቹና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎቹ  ከክልሉ መንግስት በተመደበ በጀትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ በ800 ሚሊዮን ብር መገንባታቸውን ተናግረዋል።

ለአገልግሎት የበቁት ትምህርት ቤቶችና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ከ32 ሺህ የሚበልጡ አዳዲስ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን መቀበላቸውን አመልክተዋል።

አዳዲስ የተገነቡት ትምህርት ቤቶችና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች  ከዚህ በፊት  በአንድ ክፍል ውስጥ ተጨናንቀው ይቀመጡ የነበሩ ተማሪዎችን ቁጥር በማሳነስ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያላቸውን ተጋላጭነት እንደሚቀንሱም ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የተማሪ ክፍል ጥምርታን በማስተካከል ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አጋዥ እንደሚሆኑም  ጠቁመዋል፡፡

በጎባ ከተማ ቱሉ ዲምቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችው ቢፍቱ ሀሰን “መንግስት ትምህርት ቤቶችን በመገንባት በፈጠረልን ምቹ ሁኔታ ከኮቪድ ስጋት ነጻ ሆነን ትምህርታችንን ያለምንም ስጋት እየተማርን እንገኛለን” ብላለች፡፡

በአንድ ክፍል ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማድረግ ተራርቀን መቀመጣችን ለኮቪድ-19 ያለንን ተጋላጭነት በመቀነስ ተረጋግተን ትምህርታችንን እንድንከታተል እያገዘን ነው ያለው ደግሞ የኡርጂ በሪሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አትናፍ  ከማል ነው፡፡

በዞኑ በ2014 የትምርት ዘመን ከ391 ሺህ 674 በላይ ተማሪዎች ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተመዝግበው መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑ ታውቋል።