በባሌ ዞን ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ 220 የውሀ መሳቢያ ሞተሮች ለተደራጁ አምራቾች ተከፋፈለ

110

ጎባ ፤ ጥቅምት 11/2014 (ኢዜአ) በባሌ ዞን ስንዴን በመስኖ ለማልማት የሚያግዙ 220 የውሀ መሳቢያ ሞተሮች በማህበር ለተደራጁ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ተከፋፈለ።

የውሀ መሳቢያ ሞተሮቹ መንግስት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ  በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የያዘው ዕቅድ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልይ መሐመድ እንደገለጹት፤ የውሀ መሳቢያ ሞተሮቹ የተከፋፈሉት በ120 ማህበራት ስር ለተደራጁ 900 ለሚጠጉ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ነው፡፡

የክልሉ መንግስት በረዥም ጊዜ ብድር ያመቻቸው የውሀ መሳቢያ ሞተሮቹ አምራቹ በአካባቢው የሚገኙ  የውኃ አማራጮችን በመጠቀም በባህላዊ ዘዴ ያካሄድ የነበረውን የመስኖ ልማት በዘመናዊ መልኩ ለማጠናከር እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

የውሃ መሳቢያ ሞተሮቹ በተከፋፈሉበት ወቅት የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው፤ መንግስት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዞኑ 11 ወረዳዎች ተውጣጥተው  በማህበር ለተደራጁ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች በረዥም ጊዜ ብድር የተከፋፈሉት የውሀ መሳቢያ ሞተሮች የስራው አካል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የማህበራቱ አባላትም በመንግስት የተመቻቸላቸውን አማራጮች በመጠቀም ራሳቸውን  ለመቀየር በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የውሀ መሳቢያ ሞተሮቹን ካገኙ አርሶ አደር ተወካዮች መካከል አቶ አህመድ በከር በሰጡት አስተያየት፤  በረዥም ጊዜ ብድር የተመቻቸላቸው የውሀ መሳቢያ ሞተሮች በባህላዊ መልኩ የሚያካሄዱትን የመስኖ ልማት ለማዘመን እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡

ፓምፖቹ ውሀንና ጉልበትን በመቆጠብ  የተሻለ ለማምረት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ያሉት ደግሞ ሌላው የዕድሉ ተጠቃሚ ከፊል አርብቶ አደር ማህሙድ ሲራጅ ናቸው፡፡

በባሌ ዞን በመጀመሪያ ዙር ከ10 ሺህ 500 ሄክታር በላይ ስንዴን በመስኖ ለማልማት  ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡