የትግራይ ሕዝብ ለጥቂት የስልጣን ጥመኞች ራሱን መስዋዕት ማድረግ የለበትም

154

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2014(ኢዜአ) የትግራይ ክልል ሕዝብ ለጥቂት የስልጣን ጥመኞች ሲል ራሱን መስዋዕት ማድረግ እንደሌለበት የሠላም የክብር አምባሳደር ምዑዝ ገብረህይወት ተናገሩ፡፡

የአሸባሪው የህወሃት ቡድን የስልጣን ጥመኞች ሕጻናትን አስገድደው ለጦርነት  በማሰለፍ  እየማገዱ፤  ፈርተው ወደኋላ የሚሸሹትን ደግሞ በከባድ መሳሪያ እየጨረሷቸው እንደሆነም ገልጸዋል።

አቶ ምዑዝ ገብረህይወት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሓት ከምስረታው ጀምሮ  በትግራይ ሕዝብ ስም እየነገደ የመጣ ድርጅት ነው፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ግፍ ሲፈጽም እንደነበር አስታውሰው፤ አሁንም የትግራይ ህጻናትን ጭምር አስገድዶ በጦርነት እየማገዳቸው ይገኛል ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑ በትግራይ ህጻናት ደም ስልጣኑን ለማቆየት የሚሰራና ለትግራይ ሕዝብ ደንታ የሌለው የወንጀለኞ ች ስብስብ መሆኑንም ተናግረዋል።

የትግራይ እናቶችና አባቶች በአሸባሪ ቡድኑ ምክንያት ያለ ጧሪ ቀባሪ እየቀሩ  መሆኑን ጠቅሰው፤  ሕዝቡ ለጥቂት የስልጣን ጥመኞች ሲል ራሱን መስዋዕት እንዳያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በርካታ የትግራይ ወጣቶችን የገደሉና ያስገደሉ የአሸባሪው ህወሓት ቁንጮ መሪዎች አሁንም የትግራይ ሕዝብ በከንቱ መስዋዕት እንዲሆን እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሸባሪ ቡድኑ  በወረራ በያዛቸው የአፋርና የአማራ ክልሎች ሠላማዊ ዜጎችን በጅምላ መግደል፤ አፍኖ ማሰቃየትና ዝርፊያ  እየፈጸመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የእምነት ተቋማትን ጨምሮ የአረጋዊያን መኖሪያ ቤቶችን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ አስከፊ ግፍ እየፈጸመ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

ሕጻናትን አስገድዶ በጦርነት ከፊት በማሰለፍ እየማገደ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ምዑዝ፤  ጦርነቱን ፈርተው ወደ ኋላ የሚሸሹትንም በከባድ መሳሪያ ከኋላ ሆኖ ራሱ እየጨረሳቸው  ነው ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ጥቃትና ዝርፊያ ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አዛውንቶችን ከፊት በማሰለፍ ለጥፋት እየዳረጋቸው መሆኑ ይታወቃል።