ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ የአሸባሪው ህወሃትን ህልም ለማምከን ቆርጠን ተነስተናል

206

ጥቅምት 10/2014(ኢዜአ) ከአገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ “አሸባሪውን ህወሃት በመመከትና በመታገል ህልሙን ማምከናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ የደሴ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

አሸባሪው ህወሃት በወረራ ያልያዘውን ያዝኩ፤ ያልተቆጣጠረውን ተቆጣጠርኩ እያለ አገርና ህዝብን የማደናገር የሀሰት ወሬዎች መንዛቱን ቀጥሏል።

ከሰሞኑም የደሴና ሃይቅ ከተሞችን የያዘ በማስመሰል የሽብር ቡድኑ ሲነዛ የቆየው የሀሰት ወሬዎች ሁለቱን ከተሞች ለመያዝ ያለውን ሕልም ያንጸባርቃል።

እውነታው ግን በተቃራኒው ሆኖ የደሴ ከተማ መደበኛ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋን በማከናወን ላይ ነች።

ወጣቶቹም የአሸባሪው ህወሃት የሃሰት ወሬዎችን ጆሮ ዳባ በማለት ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ከተማቸውን ተደራጅተው እየጠበቁ ይገኛሉ።

የደሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት አንዋር እንድሪስ እንደተናገረው፤ ደሴ ከተማ በወጣቶቿ እና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ደህንነቷ ተጠብቆ መደበኛ ስራዋን እያከናወነች ነው።

የከተማዋ ወጣቶች የመከላከያ፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሌሎች የጸጥታ አደረጃጀቶች ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን አመልክቶ፤ አገርን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳውን ጠላት ለመመከትና ለማጥፋት ተጋድሎ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጿል።

የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅም ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን ነው ወጣቱ የገለጸው።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት መካሽ ካሳው እንደሚለውም፤ የደሴ ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ እንደቀጠለ ነው።

አሸባሪው ህወሃት ደሴን ተቆጣጠርኩ የሚለው የተለመደ የማደናገሪያ ፕሮፖጋንዳ መሆኑን ጠቁሟል።

አሸባሪው ህወሃት በሀሰት ወሬዎች ህዝብን ከመረበሽ ያለፈ ፊት ለፊት የሚገጥምበት አቅም እንደሌለውም ይናገራል።

ወጣቱ ለአሉባልታ ጆሮ ባለመስጠት አሸባሪውን ህወሃት ለመመከት ብሎም ለማጥፋት እየተዋደቀ ከሚገኘው የአገር መከላከያና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጎን መሰለፍ እንዳለበት ወጣት ጌታቸው ገደፋው ተናግሯል።

ወጣቶቹም ግንባር ድረስ በመሄድ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች እያደረጉት ያለውን ተጋድሎ በማገዝ ደጀንነታቸውን እያረጋገጡ እንደሚገኙም አመልክቷል።

ህብረተሰቡም ከጸጥታ ኃይሎች ጎን በመሰለፍና ለጠላት ፕሮፓጋንዳ ጆሮ ባለመስጠት አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይም አሸባሪው ህወሃት እስኪደመሰስ የሚያደርጉትን ተጋድሎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።