በማእከላዊ ጎንደር ዞን የትምህርት ግብአቶችን ለማሟላት የህብረተሰቡ ተሳትፎ እየጨመረ ነው

56
ጎንደር ነሀሴ 12/2010 በማእከላዊ ጎንደር የትምህርት ግብአቶችን ለማሟላት በሚደረግ ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ እየጎለበተ መምጣቱን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የዞኑ ህብረተሰብ ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ የቁሳቁስና የጉልበት ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑ ትልቅ ማሳያ ነው ተብሏል። የመምሪያው ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት የተማሪዎች፣ የወላጆችና የመምህራን አደረጃጀቶች የትምህርት ግብአቶችን ለማሟላት ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህብረተሰቡ ለትምህርት ስራው መጠናከር ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ከማዋጣት በሻገር ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ የጉልበትና የቁሳቁስ ድጋፍ አበርክቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ በህብረተሰቡ ተሳትፎ በ27 ትምህርት ቤቶች የሚታየውን የመማሪያ ክፍል ጥበት ለማቃለል የሚያስችሉ 195 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከአንድ ሺ በላይ የመማሪያ ክፍሎች እድሳት የተደረገላቸው ሲሆን 6ሺ ተማሪዎችን ማስተናገድ የቻሉ 3ሺ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበሮች ህብረተሰቡ ባዋጠው ገንዘብ ተገዝተው ለትምህርቱ ስራ ውለዋል፡፡ 80 በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የሚታየውን የንጹህ መጠጥ ውሃና የመጸዳጃ ቤቶች አገልግሎት ችግር ለማስወገድም 15 የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማትና 65 መጸዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም የማጣቀሻ መጻህፍትን እጥረት ለማቃለል ከ8ሺ በላይ የማጣቀሻ መጻህፍት ግዢ በማከናወን በ40 ትምህርት ቤቶቹ ለተቋቋሙ ቤተ-መጻህፍት ተሰራጭቷል፡፡ በትምህርት ቤቶች ደረጃ የተቋቋሙት የወላጅ ተማሪ መምህራን ህብረት  ህብተሰቡ በትምህርት ስራው ላይ በባለቤትነት እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን የተናገሩት የምስራቅ በለሳ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይደግ ልጃለም ናቸው፡፡ በኪንፋዝ በገላ ወረዳ የጭቅቂ ቀበሌ ነዋሪና የወላጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተሻገር ማሬ “ህብረተሰቡን በማስተባበር በቀበሌያችን በድንጋይ ላይ ተቀምጠው ይማሩ ለነበሩ ልጆቻችን ባዋጣነው ገንዘብ የመማሪያ ወንበር ገዝተን እንዲማሩ አድርገናል'' ብለዋል፡፡ የወገራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ መኳንንት ደሴ በበኩላቸው መንግስት በአካባቢያቸው ያቋቋመው ትምህርት ቤት መጻዳጃ ቤት የሌለው በመሆኑ ገንዘብ ከማዋጣት ጀምሮ የጉልበትና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ አራት ክፍል መጸዳጃ ቤት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡ በበጀት አመቱ በትምህርቱ ዘርፍ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ 280 ሺ የዞኑ ህዝብ የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የጉልበት አስተዋጽኦ በማድረግ ተሳትፎ ማድረጉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም