ባለፉት ሶስት ወራት በተካሄደ የበጎ ፍቃድና አገልግሎት ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን ተችሏል

210

ጎባ፣ ጥቅምት 10/2014(ኢዜአ) በዞኑ ባለፉት ሶስት ወራት በተካሄደ የበጎ ፍቃድና የዜግነት አገልግሎት ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስትወጪ ማዳን መቻሉን የዞኑ የባሌ ዞን ህጻናት፣ሴቶችና ወጣቶች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡:

የበጎ ፍቃድና የዜግነት አገልግሎት በህብረተሰቡ ህይወት ላይ ውጤት ያለው ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ተጠቅሷል፡፡

የዞኑ ህጻናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ህንዲያ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ በየጊዜው እየተካሄዱ የሚገኙ የበጎ ፍቃድና የዜግነት አገልግሎት ስራዎች በህብረተሰቡ ኑሮ ላይ ውጤት ያለው ለውጥ እያመጡ ነው፡፡

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድና የዜግነት አገልግሎት በዞኑ 12 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 300 ሺህ የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

በክረምቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር ከተከናወኑ መካከል የ398 አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት መልሶ ግንባታና እድሳት፣ የአረጋዊያን እንክብካቤና ለ65ሺህ ችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግ ተግባራት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።

ከበጎ ፍቃደኞች 602 ዩኒት ደም መሰብሰቡንና በሀገር ህልውና እየተሳተፉ ለሚገኙ የመከላከያ ሰራዊትና የጸጥታ አካላት ከ600 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ መደረጉንም አመልክተዋል ።

የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠትን ጨምሮ በጤና፣ በግብርናና በሌሎች ዘርፎችም የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል ።

በመርሀ ግብሩ በተከናወኑ የሰብአዊ ድጋፍና የልማት ስራዎች ከ1 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውንና ከመንግስት ካዝና ይወጣ የነበረን ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ለማዳን መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

ከመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች መካከል የጎባ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ከበደ በሰጡት አስተያየት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሊፈርስ የተቃረበው ቤታቸው በቆርቆሮ በአዲስ መልክ በመሰራቱ ከስጋት ነጻ ያደረጋቸውን አዲስ ህይወት መኖር መጀመራቸውን ተናግረዋል ።

“የተደረገልኝ ደብተር፣ቦርሳና ሌሎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች ትምህርቴን በአግባቡ እንድከታተል ረድቶኛል” ያለችው ደግሞ በዲንሾ ወረዳ የ6ኛ ክፍል ተማሪ ሀሊማ ኡስማን ናት፡፡

በዞኑ በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፍቃድና የዜግነት አገልግሎት አስተባባሪና ተሳታፊ ለነበሩ የመንግስት የዘርፍ መስሪያ ቤቶች፣ የወጣት አደረጃጀቶች፣ በጎ ፍቃደኞችና ባለድርሻ አካላት የእውቅናና የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቷል።