የኅብረተሰቡ ቸልተኝነት የኮቪድ-19ን ስርጭት አሳሳቢ አድርጎታል

104

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2014(ኢዜአ) የኅብረተሰቡ የኮቪድ-19 መከላከያዎችን ያለመተግበርና ክትባት ለመውሰድ የሚያሳየው ዳተኝነት የቫይረሱን ስርጭት አሳሳቢ አድርጎታል ሲል የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ከጥቅምት 1 እስከ 7 ቀን 2014 የነበረውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሚኪያስ ተፈሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ቀውስ ለመግታት ኅብረተሰቡ ወረርሽኙን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን እንዲተገብር አሳስበዋል።

በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየውን ቸልተኝነት ተከትሎ በሣምንቱ በኮቪድ-19 የተያዙ፣ ወደ ጽኑ ሕክምና ክፍል የገቡና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደነበረ ገልፀዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ከጥቅምት 1 እስከ 7 ቀን 2014 ባለው የአንድ ሣምንት ጊዜ 227 ሰዎች በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ተናግረዋል።

ወረርሽኙ በአዲስ አበባ 98፣ በኦሮሚያ 70፣ በአማራ 8 ፣ በሲዳማ  8፣ በደቡብ 10፣ በድሬዳዋ 10፣ በሶማሌ 20፣ በሃረሪ 2 እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ የአንድ ሰው ሕይወት መቅጠፉን ጠቅሰዋል።

በመላ አገሪቱ በሳምንቱ ምርመራ ከተደረገላቸው 52 ሺህ 424 ሰዎች መካከል 4 ሺህ 771 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ብለዋል።

በበሽታው የመያዝ ምጣኔውም በአገር አቀፍ ደረጃ ዘጠኝ በመቶ መድረሱን ነው ዶክተር ሚኪያስ የገለጹት፡፡

በቫይረሱ የተያዙ 1 ሺህ 202 ሰዎች በሕክምና ማዕከላት እንደሚገኙና ከእነዚህ መካከል 600 ያህሉ የጽኑ ሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን አክለዋል።

በኢትዮጵያ ዴልታ የተሰኘው የኮቪድ-19 ዝርያ ከተከሰተ ወዲህ በተለይ ወደ ጽኑ ሕክምና ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱ ተመላክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት 23 ሺህ 287 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው፤ በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥርም 6 ሺህ 258 መድረሱን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 359 ሺህ 881 የደረሰ ሲሆን  330 ሺህ 334 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል።