አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ፊት ለፊት ለመፋለም ተዘጋጅተናል

88

ደሴ፤ ጥቅምት10/2014 (ኢዜአ )አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በመመከት ህልውናችንን ለማስቀጠል ከሰራዊቱ ጎን ከመሰለፍ ባለፈ ፊት ለፊት ለመፋለም ተዘጋጅተናል ሲሉ የደሴ ከተማ ሴቶች ገለጹ።

የደሴ ከተማ ሴቶች የህወሃት ፕሮፓጋንዳን በማውገዝ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።

የሰልፉ አስተባባሪና በአማራ ምሁራን መማክርት የቦርድ አባል ዶክተር ሐይማኖት እሸቱ እንደገለጹት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለማንም እዝነት የሌለው "የአውሬ ስብስብ" መሆኑን በሚፈፅመው ግፍ ማረጋገጥ ተችሏል።

ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ ንጹሃን ከመግደል ባለፈ ሴቶችን እየደፈረ ንብረትም እያወደመ እንደሆነ ገልፀዋል።

"አገር አፍራሹን ቡድን ለመመከት ደጀን ሆነን ከሰራዊቱ ጎን ከመሰለፍ ባለፈ ህልውናችንን ለማስቀጠልና የሀሰት አሉቧልታ ወሬዎችን ለመመከት ፊት ለፊት ለመፋለም ቆርጠን ተነስተናል" ብለዋል፡፡

ደሴና ኮምቦልቻን ለመዝረፍና ለማውደም የቋመጠውን አሸባሪ ቡድን ለመመከት ሁሉም የሚችለውን እንዲያደርግና ህብረተሰቡን ለማነቃነቅ ሰልፉ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ ሴቶች ፌዴሬሽን አባል ወይዘሮ ዙፋን ዮሃንስ በበኩላቸው "አሸባሪው ቡድን ደሴ ገብቶ እስኪዘርፈንና ህልውናችንን እስከ ሚያጠፈው ቁጭ ብለን አንጠብቅም" ብለዋል፡፡

"የትዳር አጋሮቻችንና ልጆቻችንን መርቀን ወደ ግንባር ከመላክ ባለፈ እኛም ደጀን በመሆንና ከጎናቸው ተሰልፈን የቡድኑን ጥፋትና ግፍ በጋራ እናስቆመዋለን" ሲሉ ገልፀዋል፡፡

"ቡድኑ ጥርስ በነቀለበት የውሸት ወሬው ደሴና ሐይቅን ተቋጣጥሬያለሁ በማለት በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና ለመፍጠር ቢሞክርም አልተሳካለትም" ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን በተላላኪ አሽከሮቹ ደሴን በወሬ ሊያሸብር ጫፍ ቢድርስም በተባበረ ክንድ አክሽፈነዋል ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አሚናት አህመድ ናቸው፡፡

"እኛ ሴቶች ከትዳር አጋራችንና ልጆቻችን ጋር ተሰልፈን ቡድኑን ለመቅበርና አገራችንን ለመጠበቅ የሚጠበቅብንን ሁሉ በማድረግ እናታዊ ኃለፊነታችንን እንወጣለን" ሲሉም አስታውቀዋል።

በሰልፉ ላይ ለህልውናችን እንሞታለን፤ ሴቶች ማጉረስ ብቻ ሳይሆን መተኮስም እንችላለን፤ ወሎ ለፍቅር እንጅ ለጠላት አይንበረከክም፤ ኢትዮጵያን በጋራ እናስቀጥላላታለን የሚሉና ሌሎች መፈክሮች ተስተጋብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም