አካባቢያችንን ከወራሪ ሃይል ነቅተን እየጠበቅን ነው- የሚሊሻ አባላት

97

ጎንደር፣ ጥቅምት 10/2014 (ኢዜአ) የህወሓት የሽብር ቡድን የሚፈጽመውን ወረራና ዝርፊያ ለመመከት አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ መሆናቸውን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የምስራቅ በለሳ ወረዳ የሚሊሻ አባላት ገለጹ።

የወረዳው ህዝብ ለህልውና ዘመቻው 15 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የጥሬ ገንዘብና የስንቅ ድጋፍ ማድረጉ ተነግሯል፡፡

በወረዳው በሚሊሻነት እያገለገሉ የሚገኙ አቶ አስናቀው ተስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ አሰቃቂ በደል ከፈጸመባቸው አካባቢዎች አንዱ በለሳ ነው።

የሽብር ቡድኑ አሁን ላይ በአማራ ክልል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሴቶች ላይ እየፈጸመ ያለው አረመኔያዊ ጭፍጨፋና ግድያ ታሪክ ይቅር የሚለው አለመሆኑን አመልክተዋል።

''አሸባሪው ህወሓት የከሰረ ፖለቲካውን ጠግኖ ዳግም ወደ ስልጣን ለመመለስ በአማራ ህዝብ ላይ ሂሳብ አወራርዳለሁ በማለት የጀመረውን ወረራ ለመቀልበስ የህይወት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ'' ብለዋል፡፡

ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል የበለሳ ወረዳ ሴቶች በአላትን ጭምር በመሻር በእጃቸው ፈጭተው ህወሓትን ሲቀልቡ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ በወረዳው በሚሊሻነት እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ለውጤ መብራት ናቸው፡፡

አሸባሪው ህወሓት ይህን በመካድ ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር፣ አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ በማድረግና ንብረታቸውን በመዝረፍ በአማራ ክልል እየፈጸመ ያለውን ነውረኛ ተግባር ለመፋለም ቆርጠው መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡

''የ15 አመት ታዳጊ ወጣት እያለሁ የህወሃትን የከሸፈ ትግል ተቀላቅዬ ነበር'' ያሉት ደግሞ የወረዳው ሚሊሻ አባል አቶ ሻምበል አዳነ ናቸው።

"ነገር ግን የሽብር ቡድኑ ስልጣን ላይ በቆያባቸው 27 አመታት ለበለሳ ህዝብ ልማት ሊያመጣ ቀርቶ ከተረጂነት እንዲላቀቅ አላደረገም" ሲሉ ተናግረዋል።

''ዛሬም የበለሳ ሴቶችና ህጻናት ንጹህ መጠጥ ውሃ ፍለጋ ረዥም  ኪሎ ሜትሮች በመጓዝ እየተንገላቱ ነው'' ያሉት አቶ ሻምበል "ቡድኑ ዳግም ወደ ስልጣን ለመምጣት በአማራ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ወረራ ለመቀልበስ እስከ ህይወት መስዋእትነት እታገላለሁ" ሲሉ ገልጸዋል።

የምስራቅ በለሳ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ እንግዳው በበኩላቸው በሰቆጣ በኩል ወደ ወረዳው ዘልቆ ለመግባት ሙከራ ያደረገውን የህወሀት ወራሪ ሀይል የወረዳው ሚሊሻዎች መክተው ወደ መጣበት መመለሳቸውን ተናግረዋል።

የወረዳው ህዝብ የህልውና ዘመቻውን በመደገፍ ባደረገው የደጀንነት ተሳትፎ በጥሬ ገንዘብና በአይነት 15 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የወረዳው ወጣቶችም አስፈላጊውን መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ወስደው በአካባቢ ፀጥታ ማስከበር፤ በኬላ ፍተሻ እንዲሁም ፀጉረ ለውጦችን ተከታትሎ ለህግ በማቅረብ በኩል የተጠናከረ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

የወረዳው ህዝብ የጀመረው እንቅስቃሴ የአሸባሪው ቡድን ግብዓተ መሬት እስኪጠናቀቅ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም