ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊተላለፉ የነበሩ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ከተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ

110

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 9/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ከተማ ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊተላለፉ የነበሩ የጦር መሳሪዎች ከሁለት ተጠርጣሪ ግለሰቦች ጋር ትናንት በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ቡን ዌው ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጸት፤ የጦር መሳሪያዎች የተገኙት በጋምቤላ ከተማ ከዜሮ አንድ ቀበሌ  ወደ ቀበሌ ሶስት በባጃጅ ተሽከርካሪ ተጭነው ለሸኔ የሽብር ቡድን ለማስተላለፍ ሲሞክር ነው።

ከተጠርጣሪዎቹ ጋር በቁጥጥር ስራ ከዋሉት የጦር መሳሪያዎች መካከል አንድ ላውንቸር ፣ አንድ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ፣  76 የዲሽቃ እና 705 የክላሽንኮቭ  ተተኳሽ ጥይቶች እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪ ግለሰቦች በሰጡት ቃል ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊተላለፉ እንደነበር መናገራቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።

የክልሉና ፌደራል ፖሊስ በጋራ በመሆን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩን ለመከላከል በተደረገ ጥረት የትናንቱን   ጨምሮ  ባለፈው ሩብ የበጀት ዓመት 60 የክላሽኮሽንኮቭ እና አንድ ላውንቸር መሳሪዎች  ከ781 ተተኳሽ  ጥይቶች ጋር መያዝ መቻሉን ገልጸዋል።

የጸጥታ አካላት ከህብረተሰቡን ጋር በመቀናጀት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት እየሰሩ መሆናቸውን ነው የቢሮው  ኃላፊ የተናገሩት።

በፌደራል ፖሊስ የምዕራብ ዳይሬክቶሬት የዲቪዥን አንድ አዛዥ ምክትል ኮማንደር አንፍሬ አህመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ እየበረከተ የመጣውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመግታት ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጀት እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በዚህም ትናንት የተለያዩ የጦር መሳሪዎች ከሁለት ተጠርጣሪ ግለሶቦች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋል እንደቻሉ አረጋግጠዋል።      

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎቹ ለሸኔና ሌሎች የሽብር ቡድኖች ሊተላለፉ የነበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ይህን መሰል ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን በማጋለጥ ረገድ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም