በጎ ተጽዕኖ በሚያሳርፍ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትግበራ ላይ የተሰማሩት ተመራማሪ አንድ ሚሊዮን ዶላር አሸነፉ

85

ጥቅምት 09/2014 (ኢዜአ) በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ በጎ ተጽዕኖ በሚያሳርፍ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትግበራ ዙሪያ የተሰማሩት አሜሪካዊቷ ተመራማሪ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ማሸነፋቸው ተነገረ።

በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ የኖቤል ተስተካካይ የሚባልለትን የአንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሽልማት አሜሪካዊቷ ተመራማሪ ማሸነፋቸው ተገልጿል።

ሽልማቱ ዘንድሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን የዘንድሮ አሸናፊ ሲንቲያ ሩዲን በአሜሪካው ድዩክ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ተመራማሪ ናቸው።

በዘርፉ ለአስራ አምስት ዓመታት ሲሰሩ መቆየታቸውም የሽልማት ተቋሙ መረጃ አመላክቷል።

ማሕበራዊ ኃላፊነት የሚሰማው እና በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ቀጥተኛ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ትግበራ ዙሪያ በመስራታቸው ሽልማቱ እንደተበረከተላቸው ተገልጿል።

ተመራማሪዋ ሰዎች በቀላሉ የሚረዷቸውና እራሳቸውን መግለፅ የሚችሉ የትንበያ መላምቶችን በማበልፀግ ለዘርፈ ብዙ ማሕበራዊ አገልግሎቶች እንዳዋሉ ተብራርቷል።

በዚህም በፍትሕ ሥርዓት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና በጤናው ዘርፍ የተመራማሪዋ ስራዎች በተግባር ውለው ለተግዳሮቶች መፍትሔ መሆን መቻሉን ኢዜአ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሽልማቱ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለሰው ልጅ የተሻለ ጥቅም እንዲውል ስኩዊረል ኤአይ በተባለ የበይነ መረብ የትምህርት ተቋም የገንዘብ ድጋፍ በየዓመቱ የሚበረከት መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም