አሸባሪው ህወሃት የጀመረውን ጦርነት ለመመከት ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ

84

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሓት የጀመረውን ጦርነት ለመመከት በጦርነት ቀጣና ያሉ ዜጎች ከጸጥታ አካላት ጋር ሆነው ጥቃቱን እንዲመክቱ መንግስት ጥሪ አቀረበ።

መንግስት የሕዝቡን ዘላቂ ጥቅም የሚያስጠብቁ ተግባራትን ለመፈጸም ዝግጅቱም አቅሙም እንዳለው፣ አስፈላጊ እርምጃዎችንም እንደሚወስድ አስታውቋል።

 የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ እንደገለጹት፤ አሻባሪው ሕወሓት ሰሞኑን በደቡብ ወሎ አምባሰልና ውጫሌ እንዲሁም በአፋር ጭፍራ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍቷል።

አሻባሪ ህወሃት ጥቃት ለመፈጸም ሲመጣ ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አዛውንቶችን ከፊት አሰልፎ መሆኑን አመልክተዋል።  

አሸባሪው በብዙ ሺ የሚቀጠሩ ንጹሓንን ከፊት ሲያሰልፍ ከኋላ ረድፍ ደግሞ መለስተኛና ከባድ መሳሪያ የታጠቁትን እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

ከፊት የሚሰለፉት የሕብረተሰብ ክፍሎች በአካባቢው የደረሰ ሰብል ለመዝረፍ ‘ማጭድ’ ጭምር ይዘው እንደሚንቀሳቀሱም አውስተዋል።

በዚህ መንገድ ከ20 እና 30 ኪሎ ሜትር ላይ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ የከተማው ነዋሪ ተሸብሮ እንዲፈናቀል ማድረጉን ጠቁመው፤ ከ30 የማያንሱ ንጹሓን ዜጎችን መግደሉንም አብራርተዋል።

አሸባሪው ህወሃት አስቀድሞ በያዛቸው አካባቢዎች ሕዝቡ አካባቢውን ለቅቆ በመውጣቱ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት እየፈጸመ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

ቀደም ብሎ ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎችን በወረራ በመያዝ በርካታ ንጹሃንንና የሃይማኖት አባቶችን ገድሏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ ከብቶችን በጥይት ደብድቦ ገድሏል፣ ንብረት አውድሟል።

"ከአማራ ጋር ሂሳብ አወራርዳለሁ" በሚል በጀመረው ጥቃት በርካታ ዜጎች ላይ ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶች ፈጽሟል፤ እየፈጸመም ይገኛል።  

የመንግስትና ግል ተቋማትን ንብረቶች በመዝረፍና በማውደም በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ባዶ የሚያስቀር ዘራፊ ቡድን መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

አሻባሪው ህወሃት በተከታታይ በሚፈጽማቸው ጥቃቶች ህዝብን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ከመሆኑም በላይ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የእርዳታ እህል እንዳይደርስ ማድረጉም ይታወቃል።

መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ተግባራዊ ካደረገ በኋላ አሸባሪው ህወሃት በአጎራባች ክልሎች የተለያዩ ጥቃቶች በመፈጸም በዜጎች ላይ ከፍተኛ አካላዊና ቁሳዊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ እየተካሄደ ያለው "በከሃዲያንና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚፋለሙ ወገኖች መካከል ነው" ያሉት ዶክተር ለገሰ፤ አገሪቷ የሁሉንም ትብብር የምትፈልግበት ወቅት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

በተለይም ጦርነቱ ባለበት አካባቢ ያለ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት፣ ሴት፣ ጎልማሳ ሳይል ከጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ ጥቃቱን እንዲመክት መንግስት ጥሪ ማቅረቡን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሃት በሙሉ አቅሙ ለወረራና ለዘረፋ መምጣቱን አመልክተው፤ ዜጎች አካባቢያቸውን ሳይለቁ ሽብርተኛውን መመከት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በተለያዩ አካባቢዎች ብሔረሰቦችን ሊያጋጩ የሚችሉ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ሕዝቡ በሁሉም መስኩ ዝግጁ ሆኖ ሰላሙን መጠበቅ እንዳለበትም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ነጋዴዎች ከንግድ አሻጥር እንዲወጡ፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች የሕዝብ አገልጋዮች በስራ ላይ እንዲያተኩሩ "መንግስት ጥሪ ያቀርባል" ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ በተደራጀ መልኩ የሚመጣውንና ወታደራዊ ዒላማዎችን ማዕከል ያደረገ ጥቃት መከላከያ ሰራዊት እየመከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

መንግስትም የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ባገናዘበ መልኩ ተከታታይ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚሄድም አመልክተዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚያስጠብቁ መረጃዎችን ለሕዝብ እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል።

አሻባሪው ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የክህደት ጥቃት በመፈጸሙ ምክንያት የፌዴራል መንግስት ሕግ የማስከበር ስራ ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም