በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ የተጎዱ እንስሳትን ሕይወት ለመታደግ መኖ እየተጓጓዘ ነው

123

አዲስ አባባ፤ ጥቅምት 8/2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ የተጎዱ እንስሳትን ሕይወት ለመታደግ የመኖ ማጓጓዝ ስራ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትር ደኤታው ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት መስሪያ ቤታቸው ድርቁ መከሰቱን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመቀናጀትና የተለያዩ መኖዎችን በማሰባሰብ ለችግሩ ጊዚያዊ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

መንግስት በተለያዩ ቦታዎች ያስቀመጣቸውን ደረቅ መኖዎች ወደ ስፍራው እያጓጓዘ መሆኑንም ገልጸዋል።

ቀደም ብሎ የተጫነው የከብት መኖ ችግሩ በተከሰተበት ስፍራ መድረሱን የገለጹት ዶክተር ፍቅሩ በመጓጓዝ ላይ የሚገኝ መኖሩንም አክለዋል።

ወቅቱ እንደ ሳርና ገለባ ያሉ የከብት መኖዎች አለመድረስና ቀደም ሲል ተዘጋጅቶ የተቀመጠ በቂ የመኖ ክምችት አለመኖር ችግሩን በፍጥነት ለመመከት እንዳይቻል ማድረጉን ተናግረዋል።

እንደ አገር የከብት መኖን ለአደጋ ጊዜ አስቦ የማከማቸት ልምድ ያለመኖሩን ጠቁመው በቀጣይ እንደ የቤት ስራ እንደሚያዝ ነው የተናገሩት።

አሁን ያጋገጠመውን ድርቅ ለመቋቋም ከኦሮሚያ ክልል በየቀኑ የእንስሳት መኖ እየተጫነ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ፍቅሩ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በአካባቢው ያለውን ጉዳትና የድጋፍ አሰጣጥ ሁኔታ የሚያጠናና ምላሽ ለመስጠት የሚያግዝ ቡድን ነገ ወደ ስፍራው እንደሚጓዝም ተናግረዋል።

መኖው ከተዳረሰ በኋላ ለእንስሳቱ የክትባትና የሕክምና ስራዎች እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ለተቸገሩ ወገኖች ከ27 ሺህ 900 ኩንታል በላይ እህል መድረሱን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ትናንት መግለጹ ይታወቃል።