የፍትህ ስርዓቱ በግል ስሜት ከተነዳ አገሪቱ ፈተና ላይ ትወድቃለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ

115
አዲስ አበባ ነሀሴ 12/2010 የኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት በግል ስሜት በመነዳት አገሪቱን ፈተና ውስጥ እንዳይከታት ሁሉም ሊከላከል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ተናገሩ። "ነፃነትና ስርዓት አልበኝነትን ባለመለየት መረን የወጣ ህግና ስርዓትን የማያከብር የመንጋ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ መቆም አለበት" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በተለያዩ ሙያዎች በሁለተኛ ዲግሪና ዲፕሎማ ለተመረቁ ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት መኮንኖች ባስተላለፉት መልዕክት ነው። ከህግ የበላይነት መጣስ ጋር በተያያዘ ሊደርስ የሚችለውን አገራዊ ኪሳራ ለመግታት የህግ ልእልናን ጠንቅቆ ማወቅ፣ ማክበርና ማስከበር የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ቢሆንም የአገር መከላከያ ሰራዊት ደግሞ ድርብ ኃላፊነት ነው ሲሉም ተናግረዋል። “ህግ አልባና አመፅን የሚታገስ ስርዓት አንደአገር መቆጠራችንን ከንቱ ስለሚያደርገው አንድነታችንን በህግ አግባብ ማስጠበቅ የዘወትር ተልዕኳችን ይሆናል" ብለዋል። "ዘመናዊነት የህግ የበላይነትን ማክበር ነው፤ የህግ የበላይነትን ያላከበሩ ህዝቦች በህግ የሚገዙ አምባገነኖችን ይፈጥራሉ እንጂ አሸናፊ መሆን አይችሉም።” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። አገራዊ ወታደራዊ እሴቶችና የጀግንነት ታሪኮችን ለማጥናት፣ ምርመራ ለማድረግ የሚተጋ በሌላ በኩል ደግሞ ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ብቃት የፈጠረ፣ አቅሙ በሁሉም አውደ ውጊያ የተመሰከረለት ሰራዊት መገንባት የመንግስት ቀዳሚ ፍላጎት መሆኑንም አመልክተዋል። በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመረቋቸው ወታደሮች 130 ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ 10ሩ የውጭ አገር ዜጎች ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም