በ32 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ምርጥ ዘር እየተባዛ ነው

135

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ32 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ምርጥ ዘር እየተባዛ መሆኑ ተገለፀ።

ይህም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችለውን አቅርቦት ለማሟላት እንደሚያስችል ተገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎችና ሚኒስትሮችን ያካተተ ልዑክ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የግብርና ልማት ስራዎችን ጎብኝቷል።

ልዑኩ በኩታ ገጠም የተዘራ የስንዴ፣ የበቆሎና የጤፍ፤ የተሻሻሉ የኦቮካዶና ፓፓያ እንዲሁም የቦሎቄ ምርቶችን ተዘዋውሮ በመጎብኘት አርሶ አደሮችን አበረታቷል።

መንግስት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተሻለ ስራ እንደሚያከናውን በወቅቱ ተመልክቷል።

በክልሉ አምስት አካባቢዎች ለአርሶ አደሩ የምርት ግብዓት የሚውል ምርጥ ዘር እየተመረተ መሆኑም ነው የተገለጸው።

ይህም የምርጥ ዘር አቅርቦቱን በማስፋት የተሻለ ምርት የሚገኝበት ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስችል ተመላክቷል።

ከዚህ አኳያም በአገር ደረጃ የዘንድሮ ምርት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ነው በጉብኝቱ ወቅት የተጠቆመው።

ሚኒስትሩ የዘንድሮው የምርጥ ዘር አቅርቦት ካለፈው ዓመት ጋር ሲጻጸር 25 በመቶ ጭማሪ እንደነበረውም ገልጸዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ሀብት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደሚሉት፤ በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት በአምስት ቦታዎች በ32 ሺ ሔክታር መሬት ላይ ምርጥ ዘር እየተባዛ ነው።

እንዲያም ሆኖ የክልሉ አርሶ አደሮች እስከ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ እንደሚያስፈልጋቸው አመልክተው፤ በዚህ ዓመት ማቅረብ የተቻለው 580 ሺ ኩንታል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርጥ ዘር አቅርቦቱን ለማሻሻል የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

ለኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ናቸው።

በዚህም በክልሉ ከሚገኙ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን አርሶ አደሮች መካከል 3 ነጥብ 6 ሚሊዮኑ ወደ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ገብተዋል ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልሉ ለግብርና ምርት ትልቅ ትኩረት በመሰጠቱ በኩታ ገጠም ካለው ስ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሔክታር ውስጥ፤ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መታረሱን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።