17ሺህ 408 ስቴካ ሲጋራና ሺሻ በቁጥጥር ስር ዋለ

149

ሠመራ፤ ጥቅምት 8/2014(ኢዜአ) የአዋሽ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በኮንትሮባንድ የገባ 17 ሺህ 408 ስቴካ ሲጋራ እና ሺሻ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ   የኮንትሮባንድ መከላከል ቡድን መሪ ኢንስፔክተር አለሙ ይመር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 03-92592 (ኢት)   ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ   ትናንት መነሻውን ከድሬደዋ መስመር በማድረግ   በሲሚንቶ ስር በመደበቅ  ወደ መሀል  ከተማ ለማሳለፍ  ሲሞክር በቁጥጥር ስር የዋለ ሲጋራና  ሺሻ አንዱ ነው።  

ለተቋሙ ሰራተኞች በደረሰው   ጥቆማ በተደረገው  ክትትል  በጭሮ ከተማ በሚገኘው አልበረከቴ ኬላ ላይ እስከ አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም 5ሺህ 500 ሲጋራና 5ሺ616 ሺሻ መቆጣጠራቸውን አስረድተዋል።

ሌላው በተመሳሳይ ቀን ከመኢሶ አካባቢ 6ሺህ 292  ስቴካ  ሲጋራ በመጫን ወደ አዳማ መስመር ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 03-62070(አ.አ) የሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ  በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጉባ ቆሪቻ ወረዳ በኩል  ለማምለጥ ሲሞክር መቆጣጠር መቻሉን ኢንስፔክተር አለሙ ተናግረዋል።

መቆጣጠር የተቻለውም  የጉምሩክ ሰራተኞች ከጉባ ቆሪቻ ወረዳ ፖሊሶች ጋር በመተባበር እንደሆነ አስረድተዋል።

በሁለቱም ተሽከርካሪዎች  ሲጓጓዝ የተገኘው  ሲጋራና ሺሻ  ከ14ሚሊዮን  ብር በላይ ግምት እንዳለው አስታውቀዋል።

በመቆጣጠሩ ስራ ላይ  የጉምሩክ ሰራተኞችና   በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላት  ላደረጉት  አስተዋጽኦ በተቋሙ ስም ምስጋና አቅርበዋል።