በኦሮሚያ ክልል የታየው ግብርናን የማዘመን ስራ ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲሰፋ ይደረጋል

72

ጥቅምት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የታየው ግብርናን የማዘመን ስራ ወደ ሌሎች ክልሎችም እንዲሰፋ ይደረጋል ሲሉ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተናገሩ።

ከፍተኛ የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎችን የያዘ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ሶስት ዞኖች ግብርናን የማዘመን ስራዎችን ጎብኝቷል።

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በክልሉ ግብርና ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንደ አገር ለግብርና ትኩረት መስጠት ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ክልሉ በዚህ ሂደት ብዙ ርቀት መጓዙን ተናግረዋል።

ግብርናን የማዘመኑ ተግባር ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲሰፋ አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋልም ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት ተቋማት ለግብርናው ዘርፍ እድገት የሚሰጡትን ትኩረት እንደሚከታተልና እንደሚቆጣጠር ነው የገለጹት።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ አቶ አደም ፋራህ አመራሩ ቁርጠኛ ከሆነ ብዙ ነገር መለወጥ እንደሚቻል ማየታቸውን ተናግረዋል።

በጉብኝቱ የኦሮሚያ ክልል ለሕዝብና ለአገር የሚጠቅሙና ለሌሎች ክልሎች ተሞክሮ የሚሆኑ ስራዎችን ሰርቷል ብለዋል።

ይህ መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎች እንዲሰፋና ኢትዮጵያ የተሻለ ኢኮኖሚ እንድትገነባ እንደሚሰራም አክለዋል።

ያሉት ደግሞ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው "ዙሪያችንን በአግባቡ ካየን ብዙ ሀብት እንዳለን ያየንበት ጉብኝት ነው" ብለዋል።

በክልሉ ግብርናውን ለማዘመን ተገቢውን ትኩረት ከመስጠት በዘለለ የተለየ ቴክኖሎጂም፣ ካፒታልም ጥቅም ላይ አለመዋሉን አንስተዋል።

ውጤቱ የተገኘው ኢትዮጵያ ያላትን የውኃ ሐብት፣ ምርታማ አፈር፣ የሰው ኃብትና የአየር ንብረትን በመቀም ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ይህን መልካም ተሞክሮ በማስፋት የአገሪቷን ግብርና የማዘመን ስራ እንደሚሰራ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ቡድኑ በኩታ ገጠም የተዘሩ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የበቆሎና የገብስ ማሳዎችን እንዲሁም ከውጭ አገር ጭምር የገቡ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም