ለ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ስኬት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል

160

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7/2014 (ኢዜአ) ለ10 አመቱ ልማት እቅድ መሳካት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት በተለየ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ የውጭ ቀጥታ ኢንቨሰትመንት ማስፋፊያና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር አባቢ ደምሴ፤ እንዳሉት የ10 አመት መሪ የልማት እቅድን ለማሳካት ኢንቨስትመንትን መሳብ የተቋሙ አንዱ ልዩ ትኩረት ነው።

ኢትዮጵያ የ10 አመት የልማት እቅዷን ለማሳካት ያስቀመጠቻቸውን ግቦች በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመደገፍ በሰው ሃይል፣ በአሰራርና በኢንቨስትመንት ትውውቅ በተለየ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ከተለያዩ የዓለም አገራት ግዙፍና መካከለኛ ባለሃብቶችን በመመልመል በማምረቻው፣ በግብርና ማቀነባበሪያና ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ በተለየ የምጣኔ ሃብት ዲፕሎማሲ ይሰራል ነው ያሉት።

የኢንቨስትመንትና የንግድ ህጎች መሻሻል፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት መኖርና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ተጽዕኖ መፍጠር የዲፕሎማቶችና የዲያስፖራዎች ዋነኛ ተልዕኮ ይሆናል ብለዋል።

ለዚህም ዲፕሎማቶች የወሰዱት ስልጠና፣ እና ሚኒስቴሩ ያደረገው የፖሊሲ ክለሳ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምርቶች ተወዳዳሪና ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ በግብርናው፣ በማምረቻውና ሌሎች ዘርፎች የሚያስፈልጉ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ማምጣት ሌላኛው ትኩረት ይሆናል ነው ያሉት አምባሳደር አባቢ።

የውጭ ባለሃብቶች መዋለ ነዋያቸውን ባፈሰሱባቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች የስራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ሁኔታዎች ይመቻቻሉ።

የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በሽርክና እንዲሰሩ በማድረግ በቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደት ኢንዱስትሪውን እንዲረከቡ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

በኢንቨስትመንት ዘርፍ በቅንጅት የሚከናወኑ ስራዎች መጠናከር ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በ10 አመቱ የልማት እቅድ ባለሃብቶችን መሳብና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ከማድረግ በተጨማሪ  የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋትና ቱሪስቶችን መሳብ ጥራት ያለው የምጣኔ ሃብት እድገት ለማምጣት ሌሎች የትኩረት መስኮች ይሆናሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአገር በቀል ምጣኔ ሃብት አጀንዳዎች ላይ መሰረት ያደረገ በጤናው፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ያተኮረ የ10 አመት የልማት እቅድ አውጥታ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም