አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በአዲስ አበባ 55 ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ነው

149

ጥቅምት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ 55 ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ገለፀ።

ሥርዓተ ትምህርቱን በ2015 የትምህርት ዘመን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።

ርዕሰ መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆችን ጨምሮ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የሆኑበት 28ኛው ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባዔ 'በአዲስ ምዕራፍ አዲስ ተስፋ ለትምህርት ውጤታማነት እና ብልፅግና' በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው።

ትምህርት ሚኒስቴር በ2014 የትምህርት ዘመን በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ እንደሚጀመር መግለጹ ይታወቃል።

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የትምህርት ጥራትን ታሳቢ ያደረገና ግብረ ገብነት፣ አገር በቀል እውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የመንገድ ደህንነትና ሌሎች ትምህርቶችን ያካተተ ነው።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላት እንደገለጹት፤ የሙከራ ትግበራው በ11 የሁለተኛ ደረጃ እና በ44 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጀምሯል።

በ2015 የትምህርት ዘመን ስርዓተ ትምህርቱን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

በሙከራ ትግበራው ትምህርት በአግባቡ መድረሱ እንደሚረጋገጥ ጠቅሰው፤ የመጡ ለውጦችና መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮችን ለማየት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

አቶ ዘላለም የ2013 የትምህርት ዘመን ኮቪድ-19ን በመከላከል መማር ማሰተማሩ የተካሄደበትና ውጤት ማስመዝገብ የተቻለበት እንደነበረ አስታውሰዋል።

የተማሪዎቸ ምገባ፣ የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት ለትምህርት ውጤት መሻሻል አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም ጠቅሰዋል።

የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥና መድገም እንዲቀንስ እና መጠነ መዝለቅ እንዲያድግ አስተዋፅኦ እንዳበረከቱም አክለዋል።

የተማሪዎቸ ምገባ ለተማሪዎችና መምህራን እፎይታን የፈጠረ እንዲሁም የተማሪዎችን አንድነት ያጠናከረ መርሃ ግብር መሆኑንም አንስተዋል።

ጉባኤው በ2013 የትምህርት ዘመን የነበሩ ስኬቶችና መሰናክሎችን በመለየት በቀጣይ ስራ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚመከርበት መሆኑንም አስረድተዋል።

ባለድርሻ አካላት የተማሪዎችና የትምህርትን ውጤታማነት ለማረጋገጥ እንዲረባረቡም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በእውቀት የጎለበተ ማህበረሰብ መፍጠር ተኪ የለሽ ተግባር መሆኑንም ነው የገለፁት።

ከተማ አስተዳደሩ በ2013 የትምህርት ዘመን ብቁና አገር ተረካቢ ዜጋ ለማልማት ከሰው ኃይል ልማትና ግብዓት አቅርቦት ባሻገር ህብረተሰቡ የትምህርትን ስራ በባለቤትነት እንዲደግፍ መሰራቱን ጠቁመዋል።

የከተማ አስተዳደሩን ብልፅግና ለማረጋገጥ በትምህርት ዘርፍ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ መሰረታዊ ተግባር መሆኑንም አንስተዋል።

የትምህርት ቢሮው ትምህርትን ለማሻሻል የሚያደረገውን ጥረት ከተማ አስተዳደሩ እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም