በአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ምን ተመከረ

123

በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመምከር ትናንት ምሽት ተጠናቋል።

በተለያዩ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ለሁለት ቀናት የመከረው ስብሰባ ላይ የተሳተፉ የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ዛሬ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

በውይይቱ የተዳሰሱት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አንኳር ጉዳዮች ናቸው።

ጠንካራና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት አገራት ዘርፈ ብዙ የትብብር ግንኙነቶችን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ገልጸዋል።

"ሕብረቱ የዘርፈ ብዙ ትብብር ስትራቴጂ ቀርጾ ገቢራዊ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ በዚህም አገራት እርስ በርስና ከልማት አጋር ተቋማት ጋር ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል" ብለዋል።

አህጉሩ በአሁኑ ወቅት ኮቪድ-19 እና ድርቅን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች እንደገጠመው ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ-አፍሪካ) እና አባል አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታተ የሰጡትን ምላሽም አድንቀዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶ ሉቱንዱላ ሕብረቱ የጀመረው የለውጥ ስራ ጠንካራ እና አንድነቱ የተጠበቀ አህጉር ለመገንባት ብሎም በዓለም መድረክ ጎልቶ ለመውጣት የሚያስችል እንደሚሆን ተናግረዋል።

በቻድ መካሄድ የነበረበትን 39ኛው የሕብረቱ የስራ አስፈጸሚ ምክር ቤት ስብሰባ በአገሪቷ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ እንዲዛወር ተደርጎ ኢትዮጵያ በተገቢው የኮቪድ-19 ጥንቃቄ ስብሰባው በአካል እንዲደረግ ኢትዮጵያ ላደረገችው አስተዋጽኦም አመስግነዋል።

ከስብሰባው ጎን ለጎን በተሰጡ መግለጫዎች ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የአፍሪካ የህዋ ሳይንስ ዘርፍ አንዱ ነው።

የዘርፉን እምቅ አቅም በመጠቀም የአህጉሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ መሪዎች ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ገልጸዋል።

ኮሚሽነሯ ፕሮፌሰር ሳራ ኤኒአንግ አግቦር ኮሚሽኑ አፍሪካ በህዋ ሳይንስ ያላትን አቅም ተጠቅማ የበለፀገችና ሠላማዊ አህጉር እንድትሆን የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ስፔስ ሳይንስ ስትራቴጂ እ.አ.አ ከ2018 ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በስትራቴጂው በሳተላይት ኮሙኒኬሽን፣ የመሬት ምልከታና ሌሎች የህዋ ሳይንስ ዘርፎች መካተታቸውን ገልጸው፤ አፍሪካ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም እስካሁን በሚገባ እንዳልተጠቀመችበት አክለዋል።

ስለሆነም የህብረቱ አባል አገራት የአፍሪካን የህዋ ሳይንስ አቅም በመጠቀም የአህጉሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በአፍሪካ የምግብ ስርዓት ዙሪያም የሕብረቱ የ'ግብርናና ገጠር ልማት ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ አየር' ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ ገለፃ አድርገዋል።

አፍሪካ 60 በመቶ የሚታረስ መሬት እያላት አገራቱ በየዓመቱ የምግብ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት 45 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ ነው የተናገሩት።

ይህን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ የአፍሪካ አገራት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችላቸውን ስራዎች ማከናወን እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

ለግብርና የሚያወጡትን ዓመታዊ የገንዘብ መጠን ማሳደግ፣ እምቅ የግብርና ምርት ያለባቸውን አካባቢዎች በክላስተር በመለየት ምርታማነትን ለማሳደግ መስራትና ምርት የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ለአባል አገራቱ የግብርና ምርታማነታቸው እንዲያሳድጉ የገንዘብ፣ የቴክኒክና የፖሊሲ ማዕቀፍ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል እ.አ.አ በ2022 የሕብረቱ መሪ ሀሳብ "የተመጣጠነ ምግብና የምግብ ዋስትና" እንዲሆን የቀረበው ሀሳብ አንዱ ነው።

በሌላ በኩል በፈረንሳይ በተካሄደው 21ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የበለጸጉ አገራት ለታዳጊ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን እንዲቋቋሙ የ100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም ገንዘቡን እየሰጡ እንዳልሆነ አምባሳደር ጆሴፋ ገልጸዋል።

የበለጸጉት አገራት በሚለቁት በካይ ጋዝ ዋነኛ ተጎጂ የሆኑት በማደግ ላይ ያሉ አገራት መሆናቸውን አመልክተው፤ አገራቱ የገቡትን ቃል አለመፈጸማቸው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አመልክተዋል።

ከሕብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጎን ለጎን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከላይቤሪያ፣ ቡሩንዲ፣ አልጄሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ብሩንዲ፣ አንጎላ፣ ዩጋንዳና ቤኒን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አካሂደዋል።

የአልጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ "ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ በሆነ የሰላም አማራጭ እንዲፈታ ቁርጠኛ አቋም ያላት አገር ናት" ሲሉ ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሠላም፣ መረጋጋትና ብልጽግና እንዲሰፍንም ጉልህ ሚና እያበረከተች ነው" ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ከኢትዮጵያ ጋር የመስራት ፍላጎት ያላት አልጄሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን፤ አገራቱ በንግድ እንዲተሳሰሩም ፍላጎት እንዳላት አክለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታን ላማምራ የዓረብ ሊግ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የያዘው አቋም የተዛባና የተሳሳተ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።

የዓረብ ሊግ ለግብጽ እና ለሱዳን ያደላ አቋም መያዙን የገለፁት አቶ ደመቀ፤ "ይህንን የተሳሳተ አቋም ማስተካከል አለበት" ብለዋል።

በቀጣዩ ወር የዓረብ ሊግ ሊቀ መንበርነትን የምትረከበው አልጄሪያ ሊጉ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያለውን አቋም እንድያጤነውም ጠይቀዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታን ላማምራ በበኩላቸው አገራቸው የዓረብ ሊግ ሚዛናዊና ትክክለኛ አቋም እንዲይዝ ለማድረግ  እንደምትሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም