በኦሮሚያ ክልል ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም ታርሷል

106

ጥቅምት 6/2014(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም መታረሱን የክልሉ ኘሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንና ሚኒስትሮችን ያካተተ ልዑክ በምስራቅ ሸዋ የግብርና ምርት እየጎበኘ ይገኛል።

እስካሁንም በአደአ ወረዳ በኩታ ገጠም የተዘራ ጤፍና የአቦካዶ እርሻን ጎብኝተዋል።

ጉብኝት በተካሄደበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደገለጹት፤ በክልሉ ለግብርና ምርት ትልቅ ትኩረት በመሰጠቱ፤ በኩታ ገጠም ካለው ስድስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ፤ ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሷል።

ቀደም ብሎ ክልሉ በ2013/14 የምርት ዘመን ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት አቅዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።

ይህም ክልሉ የግብርና ምርት ሂደቱን ለማዘመን የኩታ ገጠም እርሻ በስፋት ለማከናወን አቅዶ የሚንቀሳቀስ መሆኑን እንደሚያሳይ ያመለክታል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የኩታ ገጠም እርሻ 300 ሺ ሔክታር መሬት ላይ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ወደ ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ማደግ መቻሉን አብራርተዋል።

በመስኖ እርሻ ረገድም 15 የውሃ ፓምፖችን ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት 200 ሺ ሔክታር መሬት በመስኖ መልማቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም በግብርና ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጪ ለመላክና ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራም ገልፀዋል።

ማሳቸው የተጎበኘ አርሶ አደሮችም በመንግስት እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ ከቀደመው የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን አስረድተዋል።

ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የተመራ ልዑክ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የግብርና ስራዎችን መጎብኘቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም