ለተፈናቃዮች እርዳታ አሰጣጥ ላይ ያለውን የስርጭት ችግር ለመፍታት የአሰራር ስርዓት እየተዘረጋ ነው

86

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች እርዳታ አሰጣጥ ላይ የሚነሱ የስርጭት ችግሮችን ለመፍታት የአሰራር ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች እርዳታ ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ቢሆንም የተወሰኑ ዓለም ዓቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ያህል እየሰሩ አለመሆኑም ተጠቁሟል።

መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ አሸባሪው ህወሓት አጎራባች ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸም በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፤ ከፍተኛ ቁሳዊ ጉዳትም አድርሷል።

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ እንደሚሉት፤ መንግስት ከእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች እርዳታ የሚደርስበትን የአሰራር ሥርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

በዚህም በትግራይ ክልል የነበሩ ምግብና ምግብ ነክ አቅራቢ ተቋማት በተፈቀደበት አግባብ እርዳታ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአማራና በአፋር ክልሎች ዋና ከተሞች የእርዳታ ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም መደረጉን ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል የተከፈተ ሲሆን፤ በደሴና ደባርቅም ተመሳሳይ ማዕከላት ተከፍተዋል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በጀመረው ጦርነት ሳቢያ በአማራ ክልል ከ600ሺ፣ በአፋር ክልል ከ100ሺ በላይ ተፈናቃይ መኖሩን ጠቅሰዋል።

ለተፈናቃዮች ተደራሽ ለመሆን በባህር ዳር እና በሰመራ ከተሞች የአስቸኳይ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከላት ተቋቁመው እርዳታ እየቀረበ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለተፈናቃዮች እርዳታ አሰጣጥን አስመልክቶ ለአብነትም ከ300 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙበት ደሴ የሚነሳው ቅሬታ የአቅርቦት ሳይሆን የስርጭት ችግር መሆኑንም ኮሚሽነሩ አንስተዋል።

በተለያዩ ድጋፍ ሰጪ አካላት የሚቀርበው እርዳታ በአንድ ቋት ሳይሆን በዘፈቀደ ፊት ለፊት ለተገኘ ብቻ እየቀረበ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

ችግሩን ለማረም በደሴ በሚገኘው የአስቸኳይ እርዳታ ግብረ ሃይል ውስጥ ከኮሚሽኑ ተጨማሪ ባለሙያዎችና ከክልል ከፍተኛ አመራር በማካተት ስርጭቱ ስርዓት እንዲበጅለት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎና አፋር ላይ ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ቢኖሩም ካለው ችግር አኳያ አሁንም "የእግር ጉተታዎች አሉ" ብለዋል።

እርዳታ ሰጪ ድርጅቶቹ መንግስት መድረስ በማይችልባቸው ቦታዎች የግድ መድረስ ቢኖርባቸውም መንግስት ከለከለኝ የሚል ተጨባጭ ያልሆነ ሰበብ በመፍጠር ግዴታቸውን እየተወጡ አለመሆኑን ገልጸዋል።

'የእርዳታ ድርጅቶች ሃላፊነታቸውን እንዳይወጡ መንግስት አላደናቀፈም' ያሉት ኮሚሽነር ምትኩ መንግስት ዜጎቹ እርዳታ እንዲደርሳቸው ስለሚሻ ድርጅቶቹን አግዙኝ በሚል ምቹ ሁኔታ ስለመፍጠሩ አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም