ኦብኤን የጋምቤላ ክልልን የሚዲያ ሽፋን ለማሳደግ የጀመረው ድጋፍ የሁለቱን ክልል ህዝቦች የቆየ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው

95

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 5/2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ብርድካስት ኔትወርክ/ኦብኤን/ በጋምቤላ ክልል በሶስት የብሔረሰብ ቋንቋዎች የሚዲያ ሽፋንን ለማሳደግ የጀመረው ድጋፍ የጋምቤላና የኦሮሚያ ክልል ህዝቦችን የቆየ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስታወቁ።

ኦብኤን ባለፈው ዓመት በክልሉ በሶስት የብሔረሰብ ቋንቋዎች የጀመረውን የቴሌቭዥን ስርጭት አፈጻጸም ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተገምግሟል።

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ እንደገለጹት፤ የኦሮሚያና የጋምቤላ ህዝቦች ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ነው ብለዋል።

የሁለቱን ህዝቦች የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአኝዋሃ ፣ በኑዌር እና በማጃንግ ብሔረሰብ ቋንቋዎች የጀመረው የቴሌቭዥን ስርጭት ይህንኑ የሚያጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ኦብኤን የክልሉን ጋዜጠኞች በማሰልጠንና ሙያዊ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ በማድረግ በተቋሙ ውስጥ ቋሚ ሠራተኞች እንዲሆኑ በማድረግ ጭምር ለሰጠው ድጋፍ አመስግነዋል።

በቀጣይም የሁለቱን ህዝቦች ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር የተጀመረው ስራ ይበልጥ ጎልብቶ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ብርድካስት ኔትወርክ /ኦብኤን/ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዝናቡ አስራት በበኩላቸው፤ የጋምቤላና የኦሮሚያ ህዝቦች አብረው የታገሉና ተባብረው ብዙ ችግሮችን ያሳለፉ ናቸው ብለዋል።

የሁለቱ ህዝቦች ቀደምት አባቶች ችግሮችን በጋራ ተባብረው እንዳለፉ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ይህንኑ አጠናክሮ የሚያስቀጥል ይሆናል ብለዋል።

ኦብኤን ባለፈው ዓመት በክልሉ ሶሰት የብሔረሰብ ቋንቋዎች የቴሌቨዥን ስርጭት በመጀመሩ ከፍተኛ ደስታ የተሰማው መሆኑን በመግለጽ፤ በቀጣይም በክልሉ የኮሞና የኦፖ ቋንቋዎች በተመሳሳይ መልኩ ስርጭት ለመጀመር ፍላጎት እንዳለው ዋና ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

ኦብኤን የሀገር ውስጥና የውጭን ጨምሮ በ17 ቋንቋዎች ስርጭቶችን እያካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም