አልጄሪያ የዓረብ ሊግ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ሚዛናዊና ትክክለኛ አቋም እንዲይዝ ለማድረግ ትሰራለች

85

አዲስ አበባ፣  ጥቅምት 05/2014(ኢዜአ) አልጄሪያ የዓረብ ሊግ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ሚዛናዊና ትክክለኛ አቋም እንዲይዝ ለማድረግ እንደምትሰራ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታን ላማምራ ገለጹ።

በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።

ውይይታቸውን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መግለጫ ሰጥተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከላይቤሪያ፣ ቡሩንዲ፣ አልጄሪያ፣ ዩጋንዳና ቤኒን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

አቶ ደመቀ ከአልጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታን ላማምራ ጋር ባደረጉት ውይይት የዓረብ ሊግ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የያዘው አቋም የተዛባና የተሳሳተ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።

ይህን ተከትሎም የአልጄሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግድቡን በተመለከተ ሚዛናዊና ትክክለኛ አቋም እንዲይዝ ለማድረግ አገራቸው እንደምትሰራ ይፋ አድርገዋል።

በወቅቱ የዓረብ ሊግ ለግብጽ እና ለሱዳን ያደላ አቋም መያዙን የገለፁት አቶ ደመቀ፤ "ይህንን የተሳሳተ አቋም ማስተካከል አለበት" ብለዋል።

በቀጣዩ ወር የዓረብ ሊግ ሊቀ መንበርነትን የምትረከበው አልጄሪያ ሊጉ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያለውን አቋም እንድታጤነው ጠይቀዋል።

የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታን ላማምራ በበኩላቸው፤ የዓረብ ሊግ በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ሚዛናዊና ትክክለኛ አቋም እንዲይዝ አልጄሪያ ትሰራለች ማለታቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ በተመሳሳይ ከቡሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልበርት ሺንጊሮ ጋር መምከራቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

በውይይታቸውም የቡሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የሶስቱ አገራት ብቻ መሆን የለበትም የሚል አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል።

ከላይቤሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲ ማክስ ዌል ሳ ኬማያ ጋር በነበራቸው ውይይትም አገሪቷ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ማንሳታቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

በዚህም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን በላይቤሪያ እንድትከፍት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መጠየቃቸውን አክለዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን ከዩጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄነሪ አኬሎ ኦሪያ ጋር ባደረጉት ውይይትም የሁለቱን አገራት ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዩች ላይ መምከራቸው ተነስቷል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት የኢጋድን ተቋማዊ አቅም ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

ከአገራቱ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከርና የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ፍላጎት የታየበት እንደሆነም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም