የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሽናፊ የ6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ተሞክሮን ለአፍሪካ ሀገራት አካፈሉ

71

ጥቅምት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሽናፊ የኢትዮጵያ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከ2012 ዓ.ም ወደ 2013ዓ.ም ለማስተላለፍ በተሰጠው የሕገ መንግስታዊ ትርጉም ሂደት ላይ ተሞክሯቸውን ለአፍርካ ሀገራት አካፍለዋል።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ሞዛምፒክ ማፑቶ ከጥቅምት 3-5 2014 ዓ.ም እየተካሄደ በሚገኘው 3ኛው የአፍሪካ ሕገ መንግስታዊ ሲምፖዚየም ላይ እየተሳተፉ ነው።

የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ፅ/ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ውስጥ እንደሌሎች ሀገራት ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ምርጫውን ለማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር ምን አይነት ርምጃ መወሰድ እንዳለበት የሚገልፅ የሕገ መንግስት አንቀፅም ሆነ ልምድ የለም።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት 79 የአለም ሀገራት የተለያየ ደረጃ ያላቸውን ምርጫዎች ያስተላለፉ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ መዓዛ፤ ኢትዮጵያም በዚህ ወረረርሽን ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በመሆኗ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫዋን በወቅቱ ለማካሄድ እንደማትችል ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሲታወቅ የፌደራልም ሆነ የክልላዊ መንግስታት እጣ ምን ይሆናል የሚለው ትልቅ ሕገ መንግስታዊ ጉዳይ ሆኖ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሕግ ስርዓት ውስጥ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የጠቅላይ ፍ/ቤት ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ ሶስት ከፌዴሬሽን ም/ቤት የተወከሉ፣ ስድስት ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙያቸውና በስነምግባራቸው የተመረጡ የህግ ባለሙያዎችን የያዘ 11 አባላት ያሉት በመሆኑ ልዩ ተቋም እንደሚያደርገው ገልጸው፤ “ይህም ላስተላለፈው የውሳኔ ሀሳብ ተጨባጭነትና ታሪካዊነት እንደመነሻ የሚያገለግል ነው” ብለዋል፡፡

ጉባዔው ጥልቅ ምርምር በማድረግ መፍትሄ ያስገኘበትና በሕገ መንግሥት ትርጉም ስርዓት አዲስ ታሪካዊ ምራፍ ያሳየበት የሕገ መንግስት ጊዜ እንደነበር ወይዘሮ መዓዛ ማንሳታቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል።

ሂደቱም የሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ በተሳተፉበት በቀጥታ በቴሌቭዥን ለህብረተሰቡ የደረሰ መሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ወ/ሮ መዓዛ ለተሰብሳቢዎቹ ምንም እንኳ ሙሉ ለሙሉ ከስህተት የፀዳ ነው ባይባልም ሀገራት ከኢትዮጵያ ሁኔታ ብዙ ልምድ እንደሚቀስሙ ጠቁመው፤ “የኛ የምርጫ ማራዘም ተሞክሮ ፍትሀዊ ምርጫ እንዲካሄድ ለማድረግ ትልቅ ልምድ በመሆን ባለፈው ሰኔ በተደረገው የምርጫ ሂደት ማንኛውም ምርጫ ነክ ጉዳዮች የዜጎችን የመምረጥና የመመረጥ መብት በጠበቀ ሁኔታ በህጋዊ መንገድ እንዲሄድ ስርዓት ዘርግቷል” ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም