ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱት ያለው ጫና የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት ነው

69

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱት ያለው ጫና አፍሪካን በእጃቸው በማስገባት የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት መሆኑን የመገናኛ ብዙሃን እና የፖለቲካ ባለሙያዎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በማህበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ በንቃት ተሳትፎ የሚያደርገው ጋዜጠኛ እስሌማን አባይ እና በግል የልማትና የፖሊሲ አማካሪው ደጀኔ አሰፋ ከኢዜአ ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ቆይታ አድርገዋል።

በንግግራቸውም ምእራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱት ያለው ጫና አፍሪካን በእጃቸው በማስገባት ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለማሳካት መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት የተመሰረተ መንግስት ወደ ስልጣን መምጣቱ እና የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ እንደማይሰጥ የተረዱ የውጭ ሃይሎች የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ ጫናዎችን እያሳደሩ መሆኑን ጋዜጠኛ እስሌማን አባይ ተናግሯል።

ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከእውነት ጋር የተጣላ ሀሳብና የጉልበተኛ ዓይነት ዝንባሌ እያራመዱ መሆኑንም ገልጿል።

ዓላማቸው የተዳከመች ኢትዮጵያን በመፍጠር ለእነሱ የሚጠቅምና የሚያገለግላቸው መንግስት መሰየም መሆኑንም ነው ያስረዳው።

አሸባሪው ህወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት አላስፈላጊ እና ያበቃለት ቡድን መሆኑን ምዕራባዊያን በተለያየ ጊዜ ያወጧቸው በነበሩ ሪፖርቶች ማመልከታቸውን ያስታውሳል።

አሁን ግን እነዚህ ሃይሎች ቡድኑን ወደ መደገፍ የተመለሱት የተረጋጋችና በአካባቢው ተፅእኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያ እንዳትኖር በመሻት መሆኑን አስረድቷል።

ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የበረታ ጫና የሚያደርጉት የማደግና የመልማት እምቅ አቅሟን እና ቀጣይ ተስፋዋን ቀድመው በመገመት መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የልማትና የፖሊሲ አማካሪው ደጀኔ አሰፋ ናቸው።

በኢትዮጵያ የሚታዘዝ አሻንጉሊት መንግስት አለመኖር፣ ሌብነትን የሚጠየፍ መንግስት መምጣት፣ ከቀይ ባህርና ቀጣናዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ፍላጎት ማሳደርም ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ምዕራባዊያን እንደፈለጉ ሀብታቸውን የሚመዘብሩባቸው የፈለጉትን መሪ የሚሾሙላቸው የአፍሪካ አገራት እንዲኖሩ ለማስቻል በኢትዮጵያ ላይ ጫና የመበርታቱ ዋነኛ ምስጢር መሆኑንም አክለዋል።

"እኛ የምንላችሁን እስካልሰማችሁ ድረስ ስኬታችሁን መስማት አንፈልግም" ለሚሉ አገራት ጫናዎችን ተቋቁሞ በችግሮች ውስጥ አልፎ ጠንካራ ሆኖ ለመውጣት መልካም አጋጣሚ መሆኑን አቶ ደጀኔ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የእውነት ነፃ ወጥታ ጠንካራ አገር እንድትሆን በምዕራባዊያን የሚደረጉ ጫናዎችን ተቋቁሞ ሰብሮ በመውጣት የጥንካሬያችን መገለጫ መሆን አለበት ሲል ጋዜጠኛ እስሌማን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም