ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የጂኦ ፓለቲካ ግንኙነቱን በመምራት ወሳኝ አገር ሆና እንድትቀጥል ትኩረት ተደርጓል

276

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የጂኦ ፓለቲካ ግንኙነቱን በመምራት ወሳኝ አገር ሆና እንድትቀጥል ትኩረት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።


በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት አገሮችና የኢጋድ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ፍስሐ ሻውል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቁልፍ ሚና ያላት አገር ሆና ትቀጥላለች።

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር፣ ከአከባቢው አጋራት ጋር ካላት ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር አንጻር የተሻለ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን አንስተው በድምሩ ኢትዮጵያ የአከባቢውን አገራት አስተባብሮ ለመምራት የሚያስችል ጥሩ ቁመና ላይ ትገኛለች ነው ያሉት።   

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የጂኦ ፓለቲካ ግንኙነቱን በመምራት ወሳኝ አገር ሆና እንዲትቀጥል ትኩረት መደረጉን አምባሳደር ፍስሐ ተናግረዋል።   

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መርህ  "በውስጥ ሰላምና መረጋጋት ላይ የተመሰረተ ነው" ያሉት አምባሳደር ፍስሓ አሁን ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።

የውስጥ ችግሩ በቅርቡ እንደሚፈታና ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላውን የጂኦ ፖለቲካ ግንኙነት ወሳኝ አገር ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ተለዋዋጭ ጂኦ ፖለቲካ ሁነቶች የሚስተዋሉበት በመሆኑ ኢትዮጵያ የዚህ ተጽዕኖ ጉዳት ሳያደርስባት እያለፈች መሆኑንም አንስተዋል።  

ከዛም ባለፈ በአከባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በተለይም ከጎረቤት አገራት ጋር ሠላምን ለመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም ከግብጽና ከሱዳን ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እንዲሁም ከሱዳን ጋር ድንበርን የተመለከቱ አለመግባባቶች በሰላም እንዲፈቱ ኢትዮጵያ አበክራ እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።  

በተጓዳኝም ጎረቤት አገራት እርስ በእርሳቸው ሰላም እንዲሆኑ ኢትዮጵያ ውጤታማ የማሸማገል ሥራ መሥራቷን ጠቁመው ይህም አዎንታዊ ሚና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

በቅርቡ በኬኒያና በሶማሊያ መካከል ያለው የውሃ ድንበር ውዝግብም እልባት እንዲያገኝ ኢትዮጵያ አስቀድማ በጀመረችበት የውይይት ማዕቀፍ ሚናዋን ትወጣለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት ያላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በቅርቡ በመንግሥት ምሥረታው የተገኙ የአከባቢው አገራት መሪዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል ብለዋል።  

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስሩ ይበልጥ እንዲጠናከርና ቀጠናውን ለማበልጸግ በግንባር ቀደምትነት እንደምትሰለፍ አምባሳደር ፍስሐ አረጋግጠዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም