ኢትዮጵያ ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋ ከተጋለጡ ዜጎቿ መካከል 70 በመቶውን በራሷ አቅም እየረዳች ነው

73

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋ ከተጋለጡ ዜጎቿ መካከል 70 በመቶ የሚሆነቱን በራሷ አቅም እየረዳች መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
ዓለም ዓቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን ''አብሮነት ለምድራችን ደህንነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተከብሯል።

እለቱ ሲከበር አደጋ መከላከል ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነሩ ምትኩ ካሳ፤ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በአየር ንብርት ለውጥ ሳቢያ አደጋዎች እየጨመሩ መጥተዋል።

ኢትዮጵያም በዚሁ ሂደት ውስጥ ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በስፋት ስትዳረግ መቆየቷንና አሁንም መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በ1966 ዓ.ም በሰሜኑ አካባቢ የተከሰተው ድርቅ ወደ ቸነፈር ተቀይሮ 250 ሺህ ሰዎችን መቅጠፉን አቶ ምትኩ አስታውሰዋል።

ከዚህ በኋላም ላለፉት 47 ዓመታት የእርዳታ ማስተባበሪያ መስሪያ ቤት አቋቁማ ዜጎቿን እየታደገች ትገኛለች ነው ያሉት።

በአገር ደረጃ ትልቅ አቅም በመፍጠር ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎችን በመንግስት አቅም የማገዝ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በዚሁ መሰረት 70 በመቶ እርዳታ በመንግስት እየተሸፈነ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ተጨማሪ 1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለእርዳታ የሚውል ስንዴ ግዥ እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።

እርዳታ ዘላቂ ጥቅም ስለማያመጣ መንግስት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ አተኩሮ የሚሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት ኮሚሽነር ምትኩ።

እስካሁን በተሰራው የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራ እንደ አገር የተሻለ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው በዚሁ ዘርፍ ከተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ረጂ ድርጅቶች ጋር በስፋት የሚሰራ ይሆናል ብለዋል። 

በመርሃ ግብሩ ላይ የዓለም ዓቀፍና አህጉር ዓቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ተወካዮችም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዓለም ዓቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ44ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም