የአንስቴያዥያን ባለሙያዎችና ተማሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለገሱ

103

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓለም የአንስቴያዥያን ቀንን ምክንያት በማድረግ የአንስቴያዥያን ባለሙያዎችና ተማሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል፡፡
የማህበሩ አባላት የዓለም አኒስቴዢያን ቀንን በማስመልከት ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ ለመግለፅ በኢትዮጵያ ደም ባንክ በመገኘት ደም ለግሰዋል፡፡

ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ደም መለገሳቸውን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ሉአላየሁ አካሉ ገልጸዋል።

የማህበሩ አባል ረዳት ፕሮፌሰር አማረ ሀይለኪሮስ በበኩላቸው በግንባር ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ደም በመለገሳቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለ19 ጊዜ ደም መለገሳቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አኒስቴዥያን ለድንገተኛ ህክምና ቅርብ በመሆናቸው ችግሩን ከማንም በላይ እንደሚረዱት የጠቀሱት  ረዳት ፕሮፌሰሩ በማህበራቸው በኩል ሰራዊቱን በቅርበት ለመደገፍ  ግንባር ድረስ የተጓዙ አባሎቻቸው እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአንስቴያዥያን ትምህርት ክፍል የ4ኛ ዓመት ተማሪ ሜላት ከይረዲን ደም መለገስ ምንም ጉዳት ስለሌለው “ደም እየሰጠን ህይወት ማትረፍ የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል” ብላለች።

አንድ ሰው የሰጠው ደም በሶስት ወር ውስጥ ሊተካ የሚችል በመሆኑ ደም ለሚስፈልጋቸው ወገኖች ደም በመስጠት ህይወትን በመታደግ የመንፈስ እርካታ ማግኘት ይቻላል ትላለች፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአንስቴዥያን ትምህርት ክፍል የ3ኛ ዓመት ተማሪ ብሩክ ተስፋዬ፤ ለመከላከያ ሰራዊት ደም በመለገሱ መደሰቱን ገልጿል።

በተለይ ወጣቶች አገሪቷ የምትጠይቃቸውን ኃላፊነቶች በመወጣት አገር ተረካቢነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ብሏል፡፡

የዓለም አንስቴያዥያን ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን በዛሬው እለትም ደም ከመለገስ ባሻገር የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄዱ ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ መላክታል፡፡

የዓለም የአንስቴያዥያን ቀን በየዓመቱ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 16 የሚከበር በመሆኑ በነገው እለት በመላው ዓለም 175ኛ ጊዜ ይከበራል።