“ለጥናት በሚል ጫት መቃም ጀመርኩ በዚሁ ስር እየሰደደ ተደራራቢ ሱስ ሆነብኝ”

194

ጥቅምት 4/ 2014 (ኢዜአ) “ለጥናት በሚል ጫት መቃም ጀመርኩ በዚሁ ስር እየሰደደ ተደራራቢ ሱስ ሆነብኝ” የሚለው ወጣት “ሱስ የጀመረኝ ገና በ17 ዓመቴ ነው፤ ለጥናት በሚል ጫት መቃም ጀመርኩ በዚሁ ስር እየሰደደ ተደራራቢ ሱስ ሆነብኝ” ይላል በአዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ወጣት ቢኒያም የማነ ፡፡

በዚህም ላለፉት 15 አመታት የጫት የሲጋራና መጠጥ ሱሰኛ ሆኖ መቆየቱን ይናገራል፡፡

በሱሱ ምክንያት በማህበራዊ ህይወቱና በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ቀውስ አስከትሎበት እንደቆየም ነው ቢኒያም የሚናገረው፡፡

“የጫት መቃም በሂደት ለሌሎች ሱሶች መነሻ መሆኑን ወጣቶች ሊያውቁት ይገባል” ሲል የእርሱን አጋጣሚ በማንሳት ሌሎች አንዲጠነቀቁ ይመክራል።

ቢኒያም በሱስ ሳቢያ ትምህርቱን ማቋረጡን፣ ከቤተሰቦቹ ጋር ያለው ግንኙነት መበላሸቱን አስታውሶ ከሁሉም በላይ የገጠመው የህይወት መመሰቃቀል ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደከተተው ይናገራል።

ሱስ በሽታ እንጂ ፈቅደው የሚያመጡት ባለመሆኑ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው የተሳሳተ አመለካከት መስተካከል እንዳለበት ይገልፃል።

ማንኛውም ሱስ በህክምና የሚድን በሽታ በመሆኑ ታክሞ በመዳን አሁን ላይ ከየትኛውም አጉል ሱስ ነፃ መሆኑን ይናገራል።

የባሌ ጎባ ነዋሪው ጀማል ኑረዲን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ በጫትና ሲጋራ የተነሳ ወደ ሱስ በመግባቱ ለ20 ዓመታት የችግሩ ተጠቂ ሆኖ መቆየቱን ተናግሯል፡፡

በመጀመሪያ ህብረተሰቡ ሱስ በሽታ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል የሚለው ጀማል፤ ሰው ወደ ሱስ የሚገባው ፈልጎና አስቦበት ባለመሆኑ አንዴ ወደ ሱስ ከተገባ ለመውጣት አስቸጋሪ መሆኑ መታወቅ አለበት ነው ያለው፡፡

የአዲስ ህይወት የሱስ ማገገሚያ ማዕከል መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ይርገዱ ሀብቱ ሱስ በሽታ መሆኑ እንዲታወቅ በህብረተሰብ ውስጥ ሰፊ ስራ መሰራት አለበት ይላሉ።

በሱስ መጠቃትን ለመከላከል የሁሉም ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ሱስ ከተገባበት በኋላ በርካታ ፈተናዎችና ችግሮች ስለሚያስከትል ቀድሞ ለመከላከል ሰፊ ስራ መሰራት ያስፈልጋል ሲሉም ይመክራሉ።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የስነ አእምሮ ትምህርት ክፍል መምህር አቤል ወልደሚካኤልም ሱስን ለመከላከል በማህበረሰቡ ዘንድ ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ይላሉ።

አዕምሮን የሚያነቃቁ አደንዛዥ እፆች በሚወሰዱበት ጊዜ በዋናነት አዕምሮ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር በአካላዊና ስነልቦናዊ ተግባሮች ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን ማወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

አደንዛዥ እፅ በሚፈጥረው የአዕምሮ መነቃቃት እና አመለካከት ለውጥ በርካታ ሰዎች በመደሰት ይዝናኑበታል፤ እየቆየ ግን ከባድ በሽታና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትላል እና ጥንቃቄ ያሻል ሲሉ ይመክራሉ፡፡