ለጡት ካንሰር አጋላጭ የሆኑ ነገሮችን ቀድሞ በመረዳት መከላከል ይገባል

139

ጥቅምት 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለጡት ካንሰር አጋላጭ የሆኑ ነገሮችን ቀድሞ በመረዳት መከላከልና የህክምና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች ተናገሩ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፉና የብዙዎች ህይወት እየቀጠፉ ካሉ የጤና እክሎች መካከል አንዱ የካንሰር ህመም መሆኑ ይነገራል።

የካንሰር ህመም የተለያየ አይነትና ስያሜ ያለው ሲሆን አብዛኛው የካንሰር አይነት በቀላሉ የማይድን እና ለሞት የሚዳርግ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

የጡት ካንሰር በመጀመሪያው ደረጃ ላይ በምርመራ ከተደረሰበት ግን በአጭር ጊዜና በቀላል ህክምና የሚዳን መሆኑን ይናገራሉ።

የጡት ካንሰር ከሌሎች የካንሰር ህመሞች ሁሉ በቀላል ህክምና የሚድን ቢሆንም ተገቢው ክትትል ካልተደረገበት ግን ለሞት ይዳርጋል ይላሉ ባለሙያዎቹ።

በዘር፣ በልጅነት ወቅት የተደረገ የጨረር ህክምና፣ የወር አበባ ረዘም ላለ ግዜ ማየትና መዛባት ለረጅም ዓመታት በተከታታይ የወሊድ መከላከያ መውሰድ ለጡት ካንሰር ምክኒያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የካንሰር ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሙሉጌታ ካሳሁን ይናገራሉ።

በተጨማሪም አደንዛዥ እጽ መጠቀም በተለይም ሲጋራ ማጨስ፣ ቅባታማ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ የክብደት መጨመርና የአእምሮ ጭንቀትም ሊያጋልጥ ይችላል ይላሉ።

በኢትዮጵያ በአብዛኛው ለጡት ካንሰር ተጋላጮች እነዚህን ምክኒያቶች በበቂ ሁኔታ ባለመገንዘባቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የቤተሰብ ስፔሻሊስትና የጽኑ ህሙማን ክብካቤ ማዕከል ኃላፊ ዶክተር ሴና ዱጋሳ፤ የጡት ካንሰር እንደሌሎች ካንሰሮች ቶሎ ምልክት የማያሳይ በመሆኑ በተለይም የጡት ካንሰርን ለመከላከል በየጊዜው ክትትል ማድረግ ይገባል ብለዋል።

አንዲት ሴት በየወሩ አልያም የወር አበባ መጥቶ ከሄደ ከአምስት ቀን በኋላ በጡቷ ላይ የተለየ ነገር ካለ መፈተሽ እንዳለባት መክረዋል።

በኢትዮጵያ የቅድመ መከላከል ስራዎች ባለመተግበራቸው የጡት ካንሰር ህመም አሁን ላይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

በሽታውን ለመከላከል የጤና ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የጡት ካንሰር ከ20 ዓመት ጀምሮ ያሉ ወጣቶች ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰት ሲሆን 40 ዓመትና ከዚያ በላይ ባሉት ላይ ግን በስፋት የመከሰት እድል እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ።

በመላው ዓለም በየዓመቱ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ሴቶች  ለጡት ካንሰር እንደሚጋለጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም