የአህጉሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የመሪዎች ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው

84

አዲስ አበባ ጥቅምት 04/2014 (ኢዜአ) በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም የአህጉሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ መሪዎች ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ገለጹ።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ከስብሰባው በተጓዳኝ በአፍሪካ ህብረት ስር የሚገኙ የተለያዩ ኮሚሽነሮች ባከናወኗቸው ስራዎች ዙሪያ መግለጫ እየሰጡ ይገኛሉ።

በዚህም መሰረት የአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ሳራ አኒአንግአግቦር በፓንአፍሪካ የበይነመረብ ዩኒቨርሲቲና የአፍሪካ ስፔስ ሳይንስ ስትራቴጂ ባላቸው አፈፃፀም ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽኑ አፍሪካ በህዋ ሳይንስ ያላትን አቅም ተጠቅማ የበለፀገችና ሰላማዊ አህጉር እንድትሆን የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ከእነዚህም ውስጥ የአፍሪካ ስፔስ ሳይንስ ስትራቴጂ እ.አ.አ ከ2018 ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በስትራቴጂው በሳተላይት ኮሙንኬሽን፣ የመሬት ምልከታ እና ሌሎችም የህዋ ሳይንስ ዘርፎች ተካተዋል ብለዋል።

አፍሪካ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም እስካሁን በሚገባ እንዳልተጠቀመችበት ገልፀዋል።

የህብረቱ አባል አገራት ለህዋ ሳይንስ ዘርፍ ያላቸው ትኩረትና ቁርጠኝነት በሚፈለገው መልኩ ያለመሆኑ ለዚህ እንደምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ስለሆነም የህብረቱ አባል አገራት የአፍሪካን የህዋ ሳይንስ አቅም በመጠቀም የአህጉሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

የፓን አፍሪካ በየነመረብ ዩኒቨርሲቲ በካሜሮን መዲና ያውንዴ እ.አ.አ በ2019 ስራ መጀመሩን አስታውሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት 2 ሺህ 700 ተማሪዎችን በበይነመረብ እያስተማረ እንደሚገኝም አክለዋል።

በትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መስክ ከመማር ባሻገር ተማሪዎቹ ጥናት ምርምር እያካሄዱ ይገኛሉም ብለዋል።

የፓን አፍሪካ በይነመረብ ዩኒቨርሲቲና የአፍሪካ ስፔስ ስትራቴጂ የአጀንዳ 2063 አንድ አካልና በአጀንዳው የበለፀገችና ሰላማዊ አፍሪካን ለመፍጠር የተያዘውን ውጥን ለማሳካት የሚያስችሉ እንደሆኑም አስረድተዋል።

አፍሪካውያን የበለፀገች አህጉር ለመፍጠር ከቃል ባለፈ ተግባራዊ ቁርጠኝነት በማሳየት በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም