ከሀዋሳ ከተማ ዕድገት ጋር የሚመጥን ልማት ለማከናወን ቀልጣፋ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን ማስፈን እንደሚገባ ተጠቆመ

80

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 03/2014 (ኢዜአ) የሀዋሳ ከተማን ዕድገት የሚመጥን የልማት ሥራ ለማከናወን ቀልጣፋ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን ማስፈንና ህገ-ወጥ አሰራርን መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ።

የከተማዋ  አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን በገቢ መሰብሰብ ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሀዋሳ አካሂዷል።

የንቅናቄ መድረኩን የመሩት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር  ምክትል ከንቲባና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚልኪያስ በትሬ ፤ አስተዳደሩ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተከናወነ የሚገኘው የሀዋሳ ሀይቅ ዳርን የማስዋብ ፕሮጀክት፣ የታቦር ተራራ ልማት ሥራና ሌሎች ፕሮጀክቶች  እንዳሉ ጠቅሰዋል።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ከፍጻሜ ለማድረስ የገቢ አቅምን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሚልኪያስ፤ ሕገ-ወጥ አሰራርን መከላከልና የተቀላጠፈ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የከተማዋን ዕድገት የሚመጥን የልማት ስራ ለማከናወን  ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ፣ ግብር ከፋዮችም በታማኝነት መክፈል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ ተፈሪ በበኩላቸው፤ ባለፈው ዓመት ሁለት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን መሰብሰቡን አስታውሰዋል።

በተያዘው የስራ ዘመን ደግሞ ለመሰብሰብ ከታቀደው 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ውስጥ ባለፉት ሶስት ወራት ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን  ገልጸዋል።

''ከተማዋ ባላት አቅም ልክ ገቢ እየተሰበሰበ አይደለም'' ያሉት አቶ ታምሩ ፤ የግብር ስወራና ማጭበርበር እንዲሁም በደረሰኝ አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ዋንኛ ማነቆዎች እንደሆኑ አስረድተዋል።

ከግብር ከፋዮች ጋር ከተለመደው የአሳዳጅና ተሳዳጅ ግንኙነት በመውጣት ተጋግዞ ለመስራት የሚያስችል መግባባት ለመፍጠር  የንቅናቄ መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን የማዘመን እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ግብር ከፋዮችን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የመናክ አዲስ ሞተርና ባጃጅ መሸጫ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መድኃኒት ታደሰ ''ከተማ አስተዳደሩ ከኛ ጋር ተቀራርቦ መስራቱ የተሻለ ግንዛቤ እንዲፈጠርና በመካከላችን መልካም ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል'' ብለዋል።

ከግብር ከፋዩ የሚጠበቀውን ግብር በአግባቡና በታማኝነት በመክፈል ከተማ አስተዳደሩ ለሚያከናውነው የልማት ሥራ እገዛ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በብድርና እርዳታ ሰበብ ከሚቃጣባት የውጭ ጫና እንድትላቀቅ የውስጥ ገቢን ማሳደግ ቁልፍ ስራ ሊሆን እንደሚገባ  ያመለከቱት ደግሞ  የግብር ከፋዮች የሂሳብ ባለሙያና አማካሪ አቶ ታደሰ ሽፈራው ናቸው።

ለተግባራዊነቱም ሁሉም አካል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም